መንግሥቱ ጎበዜ
ክፍል አንድ
ከ15 ዓመት በፊት የካቶሊክ ቄስ የሆነ አንድ ፈረንሳዊ ተመራማሪ ከቅዱስ ላሊበላ አብያተክርስቲያናት አንዱ በሆነው በቤተ ጎልጎታ ተቀምጠን አንድ ጥያቄ ጠየቀኝ። ጥያቄው “ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ በሌሎቹ አካባቢዎች ፈቅደው በቅዱስ ላሊበላ አብያተክርስቲያናት አቅራቢያ የአርኪኦሎጅ ጥናትና ምርምር ማድረግ ግን ከልክለዋል ይኸ ለምን ይመስልኻል የሚል ነበር”። የመሰለኝን መልስ ለመስጠት እያሰላሰልኩ ሳለ እርሱ ፈጠን ብሎ “ምን መሰለህ በላሊበላ አብያተክርስቲያናት አካባቢ ቁፋሮ ከተደረገ የንጉሥ ላሊበላ አጽም ቢገኝና ንጉሡም እንደሚባለው ሆኖ ባይገኝ እስካሁን ያለውን እሳቤና ታሪክ ሊቀይር ስለሚችል ያንን ፈርተው ሊሆን ይችላል አለኝ”። እኔም በወቅቱ በሰውየው መሰሪ ንግግር ተበሳጭቸ የተናገርኩትን አላስታውሰውም።
የዚያ ሰው ንግግር ለረጅም ጊዜ የታቀደበት፣ እየተሠራበት ያለ ሥውር ዓላማ መሆኑ የገባኝና ለዚህ ጽሑፍ መነሻ የሆነኝ ባለፈው ወር በማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን /በዩቲዩብ/ በስፋት የተሰራጨው ቪዲዮ /ምስል ወድምጽ ቅንብር/ ነው። ይህ ቪዲዮ “A forgotten Tomb in Ethiopia contained DNA that Changes the Entire Christian Timeline” የሚል ርእስ የተስጠውና ከ25 ደቂቃዎች በላይ የዘለቀ ነው። ትርጉሙ እንደወረደ “በኢትዮጵያ የተረሳው መቃብር የDNA ውጤት አጠቃላይ የክርስትናን የታሪክ ቅደም ተከተል የሚቀይር ነው” ተብሎ ሊወሰድ የሚችል ነው።
ፊልሙ በሰሜን ኢትዮጵያ ከፍተኛ ተራሮች ወይም በላስታ ላሊበላ አብያተክርስቲያናት በተደረገው የአርኪኦሎጅ ቁፋሮ ከባዛልት ዐለት (basalt rock) የታነጸና ግጣም ያለው ቀብር መገኘቱን ይናገራል። ይቀጥልና ቀብሩ የተገኘው በፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2023 ዓ.ም ነው ይላል። በዚህ የፊልም ቅንብር መሠረት የተገኘው ቅሪት አካል ወይም አጽም የDNA ውጤት የተገኘው ግለሰብ ተራ ሰው እንዳልሆነና ይልቁንም ታዋቂና የተከበረ ቄስ ወይም ንጉሥ ሊሆን እንደሚችል ይገልጻል። ይሁንና ይህ ሰው ኢትዮጵያዊ ሳይሆን ዝርያው ከደቡብ ምዕራብ ኤስያ በተለይም ከፐርሽያ /ከዛሬዋ ኢራን/ እና በከፊል ከህንድ ሊሆን እንደሚችል ግምቱን ያስቀምጣል። ፊልሙ ያስከትልና ከምሥራቅ አፍሪካ ከተገኙ ወደ 80 የሚደርሱ የቅሪት አካል ግኝቶች ጋር ሲነጻጸር ይኸኛው የተለየ ነው ይላል። በተጨማሪም ከዚህ ሰው አጽም በተጨማሪ በሺዎች የሚቆጠር ቅሪት አካል መኖራችውንና ዘረ መላቸው (genetic make up) ከሕንድ፣ ከቻይና፣ ከቬነስ መሆኑን በድፍረት ይናገራል።
አጽሙ የተከፈነበት የሐር (silk) ጨርቅ እንደሆነና ይህ ደግሞ በዚያን ዘመን በኢትዮጵያ የማይመረት በመሆኑ በ10ኛው መቶ ክ/ዘመን ከቻይና የመጣ መሆኑን ይገልጻል። በሳይንሳዊ የዘመን ማወቂያ ዘዴ (radio carbon dating) መሠረት ይህ ሰው ክ950-1000 ዓ.ም ባለው ጊዜ የነበረ መሆኑንና ይህ ደግሞ በኢትዮጵያ የዛጉዌ ሥርወ መንግሥት የተጀመረበት መሆኑን ያስረዳል። ይህ ተገኘ የተባለው ሰው ከዛሬ አንድ ሺህ ዐመት ገደማ ከደቡብ እስያ በንግድና በሌሎች ምክንያቶች ወደ ምሥራቅ አፍሪካ በርካታ ሰዎች ገብተው ስለነበር በዚህ ምክንያት ወደ ኢትዮጵያ መምጣት መቻሉንና በጊዜ ሂደትም ኢትዮጵያዊ ሴት አግብቶ ኑሮ መመሥረቱን፣ ክህነት መያዙንና ወደ ንጉሣዊ ሥልጣን ሊመጣ መቻሉን ይተነትናል። ይህንን ታሳቢ በማድረግ የኢትዮጵያ የክርስትና መሠረት ከህንድና ከፐርሺያ ጋር አብሮ የተሰፋ መሆኑን ያብራራል።
ፊልሙ ድንቅ ጥበብ የሚታይባቸውንና ምሥጢራዊ የሆኑትን የቅዱስ ላሊበላ አብያተክርስቲያናትን ለማነፅ ግዙፍ ምጣኔ ሀብት /ኢኮኖሚ/፤ ትልቅ የገንዘብ አቅም፤ በብዙ ሺዎች የሚገምት የሰው ኃይል፤ የላቀ የኪነ ሕንጻ (architecture)፣ የስነ ዐለት (geology) እና የስነ ውሀ ፍሳሽ (hydrology) ጥበብ፣ በርካታ የዐለት መፈልፈያ መሳሪያዎችና መሰል አቅም የሚጠይቅ ስለሆነ የውጭ ድጋፍ ሳይኖር በአገሬው ሰዎች /በኢትዮጵያውያን/ ብቻ ሊፈጸም እንደማይችል ይገልጻል። በመሆኑም ይህ ተገኘ የተባለው ሰው በንግድና በሌሎች ምክንያቶች እጅግ የከበረና የአብያተክርስቲያናቱን ሥራ በዋናነት ስፖንሰር /ድጋፍ/ያደረገ መሆኑን ያስረዳል። አብያተክርስቲያናቱ ያለውጭ ድጋፍ ሙሉ በሙሉ በሀገር ውስጥ አቅምና እውቀት የታነጹ ናቸው ብሎ ማመኑ አስቸጋሪ እንደሆነ ይገልጻል።
ለዚህም ሁለት ጉዳዮችን አንስቶ በማስረጃነት ለመቅረብ ይሞክራል። አንደኛው በህንድ አገር የሚገኙ በርካታ ከዓለት ላይ የተፈለፈሉ ሕንጻዎች መኖራቸውና ከዚያ የተገኘው ተሞክሮ የላሊበላ አብያተክርስቲያናትን ለማነጽ እገዛ ማድረጉን ይናገራል። ይሁንና ከውጮቹ በላቀ የላሊበላዎቹ ምጡቅ የሕንጻ ጥበብ የሚታይባቸው ምናልባት እነዚህ ከውጭ የመጡት ሰዎች በላሊበላ የተለየ የሒሳብ ቀመርና የተለየ የኪነ ሕንጻ እውቀት ተጠቅመው ሊሆን ይችላል በሚል ያስቀምጣል። ሁለተኛው በአስረጅነት የተጠቀሰው ደግሞ በገድለ ላሊበላ ላይ “ቀን ቀን ቅዱስ ላሊበላ ሲያንጽ ሌሊት ሌሊት ደግሞ መላዕክት ያግዙት ነበር” የሚለውን ወስደው መላዕክት የተባሉት ከውጭ የመጡ ሰዎችን ነው የሚል ድምዳሜ ላይ ይደርሳል። ይህን ሁሉ ከዘረዘረ በኋላ ይህን ሁሉ ድንቅ ሥራ ያከናወነና የገዘፈ ታሪክ ያለው ሰው ማንነቱ እሳካሁን ድረስ እንዳይታወቅ የተደረገው ሆን ተብሎ ወይንም በቪድዮው አገላለጽ “በዝምታ ሻጥር” (“conspiracy silence”) መሆኑን ይደመድማል።
በዚህ ቪዲዮ ከቅዱስ ላሊበላ አብያተክርስቲያናት በተጨማሪ የታቦተ ጽዮንን ወደ ኢትዮጵያ መምጣትና “የቄሱ ንጉሥ ዮሐንስ” (Prester John) ታሪክ ከዚህ አጽሙ ተገኘ ከተባለው ሰው ጋራ ለማያያዝ ተሞክራል። ፊልሙ የታቦተ ጽዮንን በአክሱም /በኢትዮጵያ/ መገኘትና “የቄሱ ንጉስ ዮሐንስ” በኢትዮጵያ ነግሦ ነበር የሚሉት ትርክቶች እሳካሁን ድረስ በብዙዎች እንደ አፈ ታሪክ የሚታዩ ቢሆንም በዚሁ ንጉሥ ምክንያት ሁለቱም ጉዳዮች እውነት ሊሆኑ እንደሚችሉ ግምቱን አስቀምጧል። በትንታኔው መሠረት ታቦተ ጽዮንን ያክል ትልቅ ክብር ያላትና አደጋ ውስጥ የነበረች መንፈሳዊ ቅርስ ይህ ሰው በኢትዮጵያ ተራሮች ተደብቃ እንድትቆይ ለማድረግ ይዟት መጥቶ ሊሆን ይችላል የሚል ግምቱን ሰጥቷል። “ቄሱ ንጉሥ ዮሐንስም” እንደሚባለው ሐሳባዊ (imaginary) ሳይሆን ባለጸጋና ኃያል የነበረው ይኸው ሰው ራሱ ሊሆን ይችላል በሚል መላ ምቱን ያስቀምጣል።
ይሁንና ይህን የቪዲዮ ሥሪት ስንመረምረው በብዙ መልኩ ከእውነት የራቀ፤ እርስ በርሱ የሚጋጭናና የተለዬ ትርክት ለመፍጠር ሆን ተብሎ የተቀናበረ የሴራ ድርሰት መሆኑን ለመረዳት የሚከተሉትን ነጥቦች እንመልከት።
• ለቪድዮ ቅንብሩ የተሰጠው ርእስና የተሰጠው ትንታኔ ብዙም ተዛምዶ የላቸውም። ርእሱ “የተረሳው መቃብር በኢትዮጵያ” የተባለበትም ምክንያት ግልጽ አይደለም።
• ብዙዎች የተቀባበሉትን ይህ ቪዲዮ የሥራውን ባለቤት በትክክል ማን እንደሆነ ለማወቅ አይቻልም። ፊልሙ ከተለያዩ ቁርጥራጭ ቢዲዮዎችና AI ምስሎች የተቀናበረ ይመስላል።
• በማኅበራዊ ሚዲያ ከመሰራጨቱ ውጭ ትንታኔው በምንም ዓይነት ተቀባይነትና ታማኝነት ባለው ስይንሳዊ ግኝት ወይም የምርምር መጽሔት /reputable scientific journal/ የተደገፈ አይደለም።
• መቃብሩ ወይም አጽሙ ተገኘበት የተባለው ቦታ በትክክል ወይም በድፍረት አልተገለጸም። አንዳንድ ጊዜ ከሰሜን ከፍተኛ ቦታዎች በአንዱ ነው ሲል ሌላ ጊዜ ደግሞ ከላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት በተለይም ከቤተ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን አካባቢ እንደሆነ ይገልጻል።
• መቃብሩ የተገኘው ከባሕር ጠለል በላይ አሥር ሺህ ጫማ ርዝመት /3000 ሜትር በላይ/ ባላቸው በሰሜን ኢትዮጵያ ተራሮች ነው ቢልም፤ የላሊበላ አብያተክርስቲያናት ግን የሚገኙት ከባሕር ጠለል 2400 ሜትር ከፍታ ላይ ነው።
• መቃብሩ የተገኘው በ2023 /2016-2017 ዓ. ም በኢትዮጵያ አቆጣጠር/ ቢባልም፤ ይህ ጊዜ የጦርነት ወቅት በመሆኑ በአካባቢው ምንም ዓይነት የአርኪኦሎጅ ቁፋሮ አልተደረገም።
• በቪዲዮው ላይ የሚታዩት ክዳን ያላቸው የቀብር ዓይነቶች እስካሁን ድረስ በላሊበላ አካባቢ የሚታወቁና የተለመዱ አይደለም። ይህን የሚመስል የቀብር ዓይነት እስካሁን በአካባቢው በተደረጉት የአርኪኦሎጅም ሆነ ተያያዥ የምርምር ሥራዎች አልተገኙም።
• ቅዱስ ላሊበላ የኖረበት ዘመን በDNA ውጤት ተገኘ ከተባለው የጊዜ ቀመር ጋር የሚገናኝ አይደለም። በቪዲዎው ታወቀ የተባለው ዘመን ክ950-1000 ዓ.ም ባለው ጊዜ ሲሆን፤ በታወቀ ማስረጃ የቅዱስ ላሊበላ የንግሥናና አብያተ ክርስቲያናትን ያነጸበት ዘመን ግን ከተባለው ከ150 ዓመት በላይ ዘግይቶ ከ1160ዎቹ በኋላ ነው።
• ቪዲዮው ቅዱስ ላሊበላን የዛጉዬ ሥርወ መንግሥት የመጀመሪያ ንጉሥ እንደሆነ አድርጎ ለማቅረብ ሞክሯል። ይሁንና ከቅዱስ ላሊበላ በፊት በርካታ ነገሥታት በላስታ ነግሠዋል። ቅዱስ ላሊበላ ከአሥራ አንዱ የዛጉዬ /ላስታ ዘመን/ ነገሥታት በ9ኛ ደረጃ የነገሠ እንደሆነ ይታወቃል። ለምሳሌ ቅዱስ ይምርሐነ ክርስቶስና ቅዱስ ሐርቤ ከቅዱስ ላሊበላ በፊት የነበሩ ናቸው። ከቅዱስ ላሊበላ በኋላ የነገሡት ቅዱስ ነአኩቶለዓብና ልጁ ዐፄ ይትባረክ ናቸው።
• ከታወቀው የአገራችን ታሪክ ብሎም የዘመነ ላስታ/ዘመነ ዛጉዬ/ እንደምንረዳው በ10ኛው መቶ ክ/ዘመን ከደቡብ ኤስያ /ከኢራን ወይም ከሕንድ/ ወደ ኢትዮጵያ የሕዝብ ፍልሰት አልነበረም።
• የታቦተ ጽዮን ወደ ኢትዮጵያ መምጣት ታሪክ በቅድመ ልደተ ክርስቶስ የሆነ እንጅ ከክርስቶስ ልደት በኋላ በዘመነ ዛጉዌ /10ኛው መቶ ክፍለ ዘመን/ እንዳልሆነ በግልጽ የታወቀ ነው።
• “የቄሱ ንጉሥ ዮሐንስ” ትርክት መነገር የጀመረው በ12ኛው መቶ ክ/ዘመን መግቢያ ላይ መሆኑ ዓለም የተስማማበት ሁኖ ሳለ፤ ወደ ኋላ ጎትቶ በፊልሙ በተፈጠረው የ10ኛው መቶ ክ/ዘመን ግለሰብ ጋር ለማያያዝ መሞከሩ የማይመስል ነገር ነው። በሳይንሳዊ መንገድ በቀረበው የቅርብ ጊዜ ጥናት “ቄሱ ንጉሥ ዮሐንስ” ተብሎ የሚገለጸው የታሪክ ሰው የኢትዮጵያው ንጉሥ ቅዱስ ይምርሐነ ክርስቶስ ሊሆን እንደሚችል ከፍተኛ እምነት አለ።
• በትንታኔው ምስላቸው የሚታየው ሰዎች የሚታወቁና ከተነሳው ጉዳይ ጋር የሚገናኙ አይደለም፤ ምስላቸው ከመታየቱ በቀር ምንም ነገር ሲናገሩ አይሰማም። ለምሳሌ የቀድሞው መምህር አባ ጽጌ ሥላሴ መዝገቡ /የቀድሞው የቅዱስ ላሊበላ ገዳም አስተዳዳሪ/ በተባለው ጊዜ በቦታው አልነበሩም፤ ሌሎቹም እንዲሁ።
በአጭሩ ሲቀመጥ የፊልሙ ዋና ጭብጥ ቅዱስ ላሊበላ ማለት ኢትዮጵያዊ ሳይሆን ከውጭ የመጣ የሌላ አገር ሰው መሆኑን፤ የቅዱስ ላሊበላ አብያተክርስቲያናት የታነጹት በዚህ ንጉሥ አስተባባሪነትና የገንዘብ ድጋፍ በውጭ አገር ዜጎች እንደሆነ፤ የቅዱስ ላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት ከማነጽ ባሻገር ታቦተ ጽዮንን ለተሻለ ጥበቃ ወደ ኢትዮጵያ ያመጣት ይህ ሰው ሊሆን እንደሚችልና “ቄሱ ንጉሥ ዮሐንስ” ተብሎ በታሪክ የሚታወቀው ይኸው ከውጭ የመጣውና በፊልሙ የተገለጸው ሰው ሊሆን እንደሚችል በሰዎች አእምሮ ውስጥ ማስረጽ ነው። የዚህ ፊልም ዓላማ ታሪኩን ቀድሞ ፈጥሮ ማስረጃ ፍለጋ እንደመሄድ ያለ ነው። ታሪክ በማስረጃ ተድግፎ ይጻፋል እንጅ፤ ታሪክ ተጽፎ ማስረጃ አይፈለግም። ታሪኩም ማስረጃ ተብሎ የቀረበውም የፈጠራ ድርሰት ሲሆን ሊፈጠር የታሰበው ምስልና ሴራው ምን ያህል የገዘፈ እንደሆነ እንገነዘባለን።
ፊልሙ ሀሰተኛ ድርሰት በመፍጠር ወርቅማ የታሪክ ኩነቶችን በመውሰድ ኢትዮጵያንና የኢትዮጵያን ቤተክርስቲያን ታሪክ ዓልባ የማድረግ ስውር ደባና አደገኛ አካሄድ መገለጫ ነው። “ከሞኝ ጓሮ ሞፈር ይቆረጣል” እንደሚባለው ቀደምት አያቶቻችችን ሠርተውና ጠብቀው ለትውልድ ያሻገሩትን ድንቅ የታሪክ ቅርሶቻችንና መለያ ምልክቶቻችንን ለመንጠቅ እየተከናወነ ያለውን ዓለም አቀፍ ስውር ዘመቻ ተረድተን ነቅተን መጠበቅ እንዲሁም ተገቢውን መልስ መስጠት ካልቻልን ነገ ከነገ ወዲያ ራቁታችን እንድሚያስቀሩን ሳይታለም የተፈታ ነው።
ይቆዬን
የዚህ ጽሐፍ ዓላማ የቪድዮውን ይዘት ማስገንዘብ ሲሆን ዝርዝር ታሪካዊ ጉዳዮችን በሚቀጥለው ክፍል እመለስበታለሁ።
በዚሁ አጋጣሚ “The Church and the Crown in Ethiopia: A Historical Journy” የሚለውን መጽሐፌን ብታነቡ ብዙ ታተርፉበታላችሁ፤ የእውነተኛውን የታሪክ ማንነታችሁን ታውቁበታላችሁ።
Blogger Comment
Facebook Comment