ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
👉 ከቀናት በፊት አሜሪካ የሰው ሀገር ሉዓላዊነትን በመዳፈርና በመጣስ ልክ በራሷ ወንጀለኛ ዜጋዋ ላይ መውሰድ በምትችለው እርምጃ አግባብ በቬንዙዌላ ላይ ወታደራዊ ኦፕሬሽን አካሒዳ መሪዋን አንቃ ይዛ መውሰዷ ይታወሳል። ይሄ ነገር አሜሪካ በቀጣይ ጊዜያት ያስቸገሯትን ሀገራት መሪዎችን በዚህ ዓይነት አካሔድ በመድፈርና መንግሥታቶቻቸውን በመቀየር አንጡራ ሀብታቸውን ለመበዝበዝና ለመዝረፍ ቆርጣ መነሣቷን የሚያሳይ ሁነት ነው‼️
📌 በእርግጥ እንዲህ ዓይነቱ የአሜሪካ ሕገወጥ እርምጃ አዲስ አይደለም። በኢራቅ፣ በሊቢያ ወዘተርፈ በእኛም ሀገር ላይ ሳይቀር ስትፈጽመው የቆየችው ሕገወጥ እርምጃ ነው። ቢያንስ ግን በኢራቅ ላደረገችው ነገር የሳዳም ሁሴን በሌለ አቅም የተሰነዘረ የአጠፋቹሃለሁ ዛቻ ምክንያት ነበራት፣ በሊቢያም አል ጋዳፊ ለአሸባሪዎች የሚያደርገው ሁሉ አቀፍ ድጋፍ ምክንያት ነበራት። ቬንዙዌላ ላይ ግን የቬንዙዌላን አስጎምጅ የተፈጥሮ ሀብቶችን ለመዝረፍ ካሰፈሰፈችበት ፈጦ ከሚታይባት ወይም ልትደብቀው ካልቻለችው ምክንያት ውጭ ምንም ሊመስል የሚችልና ተጨባጭነት ያለው ምክንያት ማቅረብ አልቻለችም። በቬንዙዌላ ላይም ቢያንስ የሐሰተኛ ምክንያት ጠቅሳለች። አሜሪካ እኮ በእኛ ሀገር ጃንሆይን በደርጎች ስታስገለብጥ የምታቀርበው ምክንያት ስላልነበራት ከመፈንቅለ መንግሥቱ ጀርባ ያለችው እሷ መሆኗን እንኳ መግለጥ አልፈለገችም ነበር። ከዚህ ከተሳካው መፈንቅለ መንግሥት በፊት ከከሸፈው የ1953ዓ.ም. መፈንቅለ መንግሥት ጀርባ አሜሪካ መኖሯ በግልጽ የሚታወቅ ነገር ነው። አሜሪካ ያመጣችው ደርግ ሲሸሻት ደግሞ ወያኔንና ሸአቢያን አደራጅታ በማታገል ደርግን ስታስገለብጥም የሰጠችው ምክንያት ልክ በዓለማችን ላይ የምትደግፋቸው አንባገነን መንግሥታት እንደሌሉ ሁሉና ለኢትዮጵያ ሕዝብም እንደምታስብ ሁሉ "ደርግ አንባገነን መንግሥት ነው!" የሚል ምክንያት ነበር የሰጠችው። የተካቻቸው የወያኔና የሸአቢያ መንግሥታት ግን ከባንባገነንነትም በላይ ጭራሽ የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ ፈጻሚ (Genociders) ናቸው። እነሱን ግን እንደዚህ ስለሆኑ "ለፍርድ አቀርባቸዋለሁ!" ስትል ተሰምታ አታውቅም። ምክንያቱም የሚፈጽሙት የእሷን ፍላጎትና ዓላማ ነውና። ስለዚህ አሜሪካ ጉዳይዋ እንደ ታላቋ ብሪታንያ በግዛቷ ፀሐይ አትጠልቅም የሚያስብልን ግዛት በዓለም እውን የማድረግ ድብቅ ህልሟን ተፈጻሚ የሚያደርጉላትን ለራሷ ታዛዥና አገልጋይ አሻንጉሊት አገዛዞችን በየስፍራው ማግኘቷን ነው እንጅ አገዛዞቹ ምንም ቢሆኑ ግድ አይሰጣትም ማለት ነው። ብንዘረዝረው ጊዜ ይወስድብናል እንጅ አሜሪካ በመላው ዓለም ያላት የሀገር ለሀገር ግንኙነት ወይም የዲፕሎማሲ ሬከርድ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳየው ይሄንን ነውሯን ነው። አሜሪካ የሰብአዊ መብት ገፈፋ ጉዳይና የወንጀለኛ መሪ መኖር ጉዳይ የሚያሳስባት ቢሆን ኖሮ ሩቅ ሳንሔድ ኢትዮጵያ ውስጥ በሕዝብ ላይ የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ የሚፈጽም የወያኔ/ኢሕአዴግ ወይም የብልጽግና አገዛዝ እያለ በዲሞክራሲያዊ መንገድ ተመርጦ ሥልጣን የያዘውንና ሕዝብን አክብሮ በሕዝብም ተከብሮ የሚኖረውን ፕሬዚደንት ኒኮላስ ማዱሮን የቬንዙዌላን ሉዓላዊነት ጥሳ ሔዳ እንደ ተራ ወንጀለኛ አንቃ ባልወሰደች ነበር‼️
☝️ በነገራችን ላይ ዶናልድ ትራምፕ በግልጽ በአደባባይ ያለምንም ሃፍረት በዓለም አቀፍ ሚዲያ ላይ የቬንዙዌላን በክምችቱ በዓለም ተወዳዳሪ የሌለውን የነዳጅ ዘይት ሀብቷን ጨምሮ ሌሎች የተፈጥሮ ሀብቶቿን ሁሉ "የአሜሪካ ነው!" ብሎ መናገሩን ሰምታቹሃል አይደል??? ይሄንን ብቻ አይደለም "ካናዳንና ግሪን ላንድን የአሜሪካ ግዛት አደርጋለሁም!" ብሏል። ትራምፕ ወደእኛም በማነጣጠር "የዓባይ ግድብ የተገነባው የአሜሪካ መንግሥት በሰጠው ገንዘብ ነው!" ማለቱን ታስታውሳላቹህ አይደል??? በነገራችን ላይ የዓባይ ግድብ የተገነባው እንኳን በአሜሪካ ገንዘብ ሊሆን ይቅርና አቶ አብይ "95% በመንግሥት ገንዘብ ነው የተገነባው የሕዝቡ ድርሻ 5% ነው!" ያለውም እንኳ ሙሉ በሙሉ ሐሰት ነው። የዓባይ ግድብ የተገነባው ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያ ሕዝብ ገንዘብ ነው መንግሥት ተብየው 1% እንኳ አላበረከተም። የዓባይ ግድብ ብቻ ሳይሆን ሌሎችም በመገንባት ላይ ያሉ ሜጋ ፕሮጀክቶችም ጭምር እየተገነቡ ያሉት ሙሉ በሙሉ ከሕዝብ በተገኘ ገንዘብ ነው። እንዴት? የሚለውን ላስረዳቹህ። የአገዛዙን የተቀሸበ ዳታ እንዳለ ብንወስደው እንኳ ሀገራችን በዓመት ከዳያስፖራ ልጆቿ የምታገኘው remittance ሰባት ቢሊዮን ዶላር ነው። ተገንብቶ ለመጠናቀቅ ዐሥራ ሦስት ዓመት የወሰደው የዓባይ ግድብ የተገነባው በአምስት ቢሊዮን ዶላር ነው። ይሄ ማለት የዓባይ ግድብን የአንድ ዓመቱ remittance ብቻ ገንብቶት ሁለት ቢሊዮን ዶላር ይተርፋል ማለት ነው። አገዛዙ ሆየ ምን አደረገ መሰላቹህ ታዲያ ዳያስፖራ ወገኖቻችን ለቤተሰብ ወገኖቻቸውና ለተለያዩ ጉዳዮች ወደ ሀገርቤት በውጭ ምንዛሬ ገንዘብ ሲልኩ አገዛዙ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ አቅም በማይፈቅደው ሁኔታ የኢትዮጵያ ብር ኖቶችን እንደፈለገ እያተመ በዚህ እንደፈለገ በሚያትመው የብር ኖት የዳያስፖራውን የውጭ ምንዛሬ መንዝሮ ለተላከላቸው ቤተሰቦች በመስጠትና የውጭ ምንዛሬውን ወደራሱ ካዝና በማስገባት በዚህ ከገበያ ውጭ በሆነ መንገድ በተመነዘረ የውጭ ምንዛሬ ነው አገዛዙ የዓባይን ግድብ የገነባው። ለዚህም ነው የተገነባው ሙሉለሙሉ በሕዝብ ገንዘብ ነው የምላቹህ። ምክንያቱም አገዛዙ ከገበያ ሥርዓት ውጭ ወይም ደግሞ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ሊያንቀሳቅሰው ከሚችለው ወይም ከሚገባው የብር ኖት በላይ አገዛዙ ገንዘብ እንደፈለገ እያተመ ወደገበያ በማስገባቱ የብር የመግዛት አቅም በከፍተኛ ደረጃ አሽቆልቁሏል በዚህም ምክንያት ከፍተኛ የሆነ የኑሮ ውድነት ተከስቷል። ማን ተጎዳ ማለት ነው??? ሕዝቡ ነው የተጎዳው። ሕዝቡ የተላከለትን ገንዘብ እንደፈለገ በመታተሙ ምክንያት የመግዛት አቅሙ በእጅጉ በተዳከመ ብር ተለውጦ ወይም ተመንዝሮ ስለተሰጠው ነው ተጎጅ ሊሆን የቻለው። በመሆኑም አገዛዙ በምንዛሬው ማግኘት የሌለበትን ከፍተኛ ጥቅም አስገብቷል ማለት ነው። ለምሳሌ በትክክለኛው የብር ኅትመት ሥርዓት ሒደትና የውጭ ምንዛሬ አመነዛዘር ሒደት አገዛዙ ሦስት ብር ማግኘት ይኖርበት የነበረውን የብር ኖትን ከገበያ ሥርዓት ውጭ እንደፈለገ በማተሙ ምክንያት ከሐምሳ ብር በላይ ጥቅም ከሕዝቡ ነጥቆ ለራሱ አድርጓል ማለት ነው። በመሆኑም አርባ ሰባቱ ብር ወደ ሕዝቡ ኪስ መግባት ይኖርበት የነበረ ንጹሕ የሕዝብ ገንዘብ ነው የአገዛዙ አይደለም። በዚህ አላግባብ ባገኘው የሕዝብ ገንዘብ ነው የዓባይ ግድብ የተገነባውና ሌሎች ሜጋ ፕሮጀክቶችም እየተገነቡ ያሉት ነው የምላቹህ። በመሆኑም የዓባይ ግድብ እንኳን አሜሪካ በሰጠችው ገንዘብ ሊገነባ ይቅርና በአገዛዙ ገንዘብ እንኳ ጨርሶ አልተገነባም። ሙሉ ለሙሉ ባልተገባ መንገድ ከሕዝብ በተገኘ የውጭ ምንዛሬ ነው የተገነባው ነው የምላቹህ። ሕዝቡ በዚህ ሒደት በተፈጠረ ችግር ምን ያህል በኑሮ ውድነት እንደተጎዳ የምታዩት ነው። ግልጽ ሆኖላቹሃል ወይ⁉️
☝️ ይሄውላቹህ በአሜሪካን መንግሥት ውስጥ ከሰኔቱና ከሃውሱም በላይ ደግሞ ማን የበለጠ ጉልበትና ተደማጭነት አለው መሰላቹህ ፔንታገን (መከላከያ) እና ሲ.አይ.ኤ ናቸው የበለጠ ጉልበትና ተደማጭነት ያላቸው። ይሄንን ነገር ጠ/ሚ አክሊሉ ኃብተወልድ በደንብ አድርገው ጽፈውታል። ታላቁ ዲፕሎማት ጠ/ሚ አክሊሉ ኃብተወልድ ሀገራችን ከአሜሪካ ጋር በነበራት ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ግንኙነቶች ያደረጓቸውን ድርድሮች በሚያደርጉበት ጊዜ ኋይት ሃውስ ላይ ትኩረት አድርገው ሲንቀሳቀሱ ፕሬዚደንቱን ጨምሮ ኋይት ሃውሶቹ ለአክሊሉ ኃብተወልድ የሰጡት ምክር የነበረው "እኛ ችግር የለውም ተረድተንሃል ማሳመን ያለብህ ፔንታገንንና ሲ.አይ.ኤን ነው እነሱ ሳያምኑና ሳይቀበሉ እኛ ልናደርገው የምንችለው ነገር የለም እነሱን ማሳመን ከቻልክ የእኛ ነገር አያሳስብህ!" የሚል ምክር ነበር ለጠ/ሚ አክሊሉ የሰጧቸው። ታላቁ ዲፕሎማት ጠ/ሚ አክሊሉም "አሃ እንዲያ ነው እንዴ ነገሩ?" ብለው ትኩረታቸውን ፔንታገንና ሲ.አይ.ኤ ላይ በማድረግ ነው ጉዳያቸውን ሊጨርሱ የቻሉት። በUS አሜሪካ መንግሥት የፔንታገንና የሲ.አይ.ኤ ጉልበት ከሁሉም በላይ ሊሆን የቻለው አገልግሎታቸው technical በመሆኑ እነሱ ለኋይት ሃውስ ከሚሰጡት ምክር ውልፍት ማለት የማይቻል በመሆኑ ነው። እናም የUS አሜሪካ መንግሥት የሚሠራው እንደዚህ ነው። በመሆኑም ምን እያልኳቹህ ነው መሰላቹህ ፔንታገንና ሲ.አይ.ኤ ናቸው በዶናልድ ትራምፕ የእብድ ካራክተር ማድረግ የፈለጉትን ነገር እያደረጉ ያሉት ነው የምላቹህ። ለዚያም ነው ሴኔቱም ሐውሱም ዶናልድ ትራምፕ ሊስማማው የቻለውና ትራምፕ እየተነገራቸው ባላቸው ነገሮች በመከፋት ሥልጣናቸውን ተጠቅመው ትራምፕን "ከሥልጣን እናውርደው!" ያላሉት ነው የምላቹህ‼️
🤔 እናም አዎ ፈርጣማ ጉልበቷ አቅሏን ያሳታት አሜሪካ ለዓለማችን ከባድና አደገኛ ሥጋት ሆና መጥታለች ነው የምላቹህ። ይሄ ጉዳይ ውስጥ ውስጡን ወይም በበሳል የዓለማችን ፖለቲከኞች ዘንድ የማይታወቅ ጉዳይ አይመስለኝም በሕዝብ ዘንድ ግን ገና ከዚህ በኋላ ነው እየታወቀ የሚመጣው። የሦስተኛው ዓለም ጦርነትም የሚቀሰቀሰው አሜሪካ "ዓለምን ጠቅልየ ቅኝ ለማድረግ ላለኝ ፍላጎትና ዓላማ እንቅፋቶቸ ናቸው!" የምትላቸውን ሩሲያንና ቻይናን አንዳች ነገር አድርጌ ከመንገዴ አስወግዳቸዋለሁ ብላ ስትንቀሳቀስ ነው የሚሆነው። እሱም በቅርብ ጊዜ የሚሆን ይመስለኛል ሩቅ የሚሆን አይመስለኝም። ዕድሜ ይስጠንና ሁሉንም የምናየው ይሆናል‼️
Blogger Comment
Facebook Comment