ኦርቶዶክሳውያን አስተውሉ የወገኖቻችን እልቂት በመግለጫ ጋጋታና በሚዲያ ተቃውሞ ብቻ አይቆምም በቆራጥነት ሁለገብ ትግል ያስፈልጋል።
"እግዚአብሔር ተዋጊ ነው ስሙም እግዚአብሔር ነው " ኦ.ዘጻ 15:3
እግዚአብሔር ግን ከማን ጋር ይዋጋል? አቻና መጠን ሳይኖረው ተዋጊ ነው ሲል ቅር ያሰኛል ። ውጊያስ የሚለው ቃል ለምን ተፈጠረ ? ጦርነት ስላለ አይደለምን? ደግሞ በራእይ 12 ፥7 ላይ " በሰማይ ሰልፍ ሆነ ሚካኤልና መላእክቱ ዘንዶውን ተዋጉ ዘንዶውም ከመላእክቱ ጋር ተዋጋ አልቻላቸውም " ይላል ። ስለዚህ ጦርነት አለ ማለት ነው ። ጦርነት የሚካሄደው ሁለት ባላንጣዎች ወይም በዳይና ተበዳይ ሲኖር ነው ። በመንፈሳዊው ዓለም ሕጋዊ ጦርነት ካለ በቁሳዊውና ፍጹም ባልሆነው ዓለም ውስጥ ጦርነትን ማውገዝና ማጣጣል ፍትሃዊ አይደለም ይህ ማለት በዳይ አካል እየጨቆነ እንዲኖር የሚፈቅድ ፍርደ ገምድልነት ነው ። በዚህች ምድር ሁሉም ባሕታዊና መናኝ እንዲሆን ቢፈቅድ ኖሮ የዚህን ዓለም ውስብስብ ምስጢር ባልፈጠረው ነበር ።
የሰው ልጅ እራሱንና ገነትን እንዲጠብቅና እንዲንከባከብ በኦሪት ዘፍጥረት 2፥15 ተጽፏል ። ገነትን ጠብቃት ሲል ሊያበላሻት ወይም ሊያጠቃት ከሚችል ነገር ተከላከላት ማለቱ ነው ። ሲከላከል ደግሞ ይገድላል ወይም ጉዳት ያደርሳል
በዘፀ 22 ፥2 ሌባ በሌሊት ወደ ቤት ሊያጠቃ ወይም ሊሰርቅ ቢመጣና ባለቤቱ ቢገድለው ከደሙ ንጹህ እንደሆነ በቀጥታ እንዲህ ይላል ። " ሌባው ቤት ሲምስ ቢገኝ እርሱ እስኪሞት ቢመታ በመታው ሰው ላይ የደም እዳ የለበትም "በማለት እራስን የመከላከልና ማንኛውም ርምጃ መውሰድ ኃጢአት እንዳልሆነ በግልጽ ይናገራል ።
እራስን መከላከል ተፈጥሮአዊ መሆኑን በበርካታ የተፈጥሮ ምሳሌዎች ማሳየት ይቻላል ። ለጃርት ወስፌን ፣ ለላም ቀንድን ፣ ለነብር ጥፍርን፣ ለኤሊ ድንጋይን ፣ ለእባብ መርዝን ፣ ለአሞራ ማንቁርትን... ለሌሎች በርካታ አራዊትና እንስሳት እራሳቸውን ከአደጋና ከጠላት የሚከላከሉበት የተለያየ ጸጋ ሲሰጣቸው እራስን መከላከል ተፈጥሮአዊ ሥርዓት መሆኑን ሲያመለክት ነው ። መጽሐፍ ቅዱስ በማቴዎስ ወንጌል 19፥19 ላይ "ባለንጀራህን እንደራስህ ውደድ " ማለቱ በመጀመሪያ እራስህን ውደድ ማለቱ ነው ። እራስህን ስትወድ እራስህን ትንከባከባለህ ትጠብቃለህ ምክንያቱም እራሳችን የራሳችን ሳንሆን ከአምላክ በአምሳሉ በአደራ የተሰጠን መቅደስ ስለሆንን እራሳችንን ከማንኛውም የምንችለው ጥቃት የመከላከል ኃላፊነት አለብን ። "ማንም አክሊልህን እንዳይወስድብህ አጽንተህ ያዝ " ራእ 3:11 ለታላቅ ክብር የታጨውንና የሚበቃውን ዋናውን መቅደስ ሰውነታችንን መንከባከብና መጠበቅ የግለሰቡ ነጻ ፍቃድ ነው ።
አብርሃም የወንድሙን ልጅ ሎጥን ማርከው ከብቶቹን በዘረፉት ወቅት ጦሩን አሰባስቦ ኮሎዶጎሞርን በጦርነት ድል ካደረገ በኋላ የልዑል እግዚአብሔር ካህን የሆነው የሳሌሙ ንጉሥ መልከጼዴቅ ሕብስትና የወይን ጠጅ ይዞለት ሲወጣና በብዙ መልኩ አብርሃምን ሲባርከው እናያለን ። ኦ.ዘፍ 14፥3-21 ይህ የሚያመለክተው እንኳን በግፍ ተበድለህ ይቅርና ከተበደለ ጎን ቆመህ ብትዋጋ በብዙ እንደምትሸለምና እንደምትባረክ ነው ። እምነትና ሃይማኖት ደግሞ ከአብርሃም በላይ ማን አለ ? እኛ ከአብርሃም አንበልጥም ። እግዚአብሔር ተዋጊ ነው ስንል በሰዎች ላይ አድሮና እኛ በምናውቀውና በለመድነው መንገድ አይነት እንጅ እሱማ በተዓምርም እንደ ሰናክሬም ጦርነትም ያደርጋል ።
በሐዲስ ኪዳንም በሉቃ 22፥36 ኢየሱስም ለደቀ መዛሙርቱ አላቸው " የሌለው ልብሱን ሸጦ ሰይፍ ይግዛ" በሁለቱም እንዲዘጋጁ አዟቸዋል። ይህ ጥቅስ በመተርጉማን በተለያየ መንገድ ቢተረጎምም ሐዋርያት ግን ሰይፍ እንደ ነበራቸው በማርቆስ 14 ፥47 ላይ ቅዱስ ጴጥሮስ የሊቀ ካህኑን ጆሮ በሰይፍ ሲቆርጠው እናያለን ። ኢየሱስ ክርስቶስ በሐዋርያቱ እጅ ሰይፍ እንዳለ አያውቅም ማለት አይቻልም ። በመንፈስ እስክናድግና ሰማያዊ ስርዓት አስኪገለጥልን ድረስ በምድር ስርዓት እንድንኖር የእግዚአብሔር ቅዱስ ፈቃድ ነው ።
መላእክት እኮ የእግዚአብሔር ኃይል የተባሉ ወታደሮች የሆኑት እግዚአብሔር ኃይል ስላጠረው ሳይሆን የፍጥረቱ ድንቅ ስራ ነው ። በሰማይ ወታደር መኖር በምድርም ወታደር እንዲኖር ሆኖአል ።
በዚህ ምድር ላይ ስንኖር ለእግዚአብሔርን የሚሆን ትውልድንም ሆነ ቤተ ክርስቲያን ለትውልድ ለማስቀጠል ዘመኑ የሚፈቅደውን እራስን የመከላከያ መንገዶችን መጠቀም ከአምላክ ከተሰጡን ነጻ ፍቃዶች አንዱ በመሆኑ በምንም መመዘኛ ኃጢአት አይሆንም ። ታዲያ ለምን ታላቋ ቁስጠንጥንያ ሰለመች? ለምን ደማስቆ ሰለመች? ለምን ግብጽና ሊቢያ ሰለሙ? የተሰጣቸውን የመከላከል እድል ስላልተጠቀሙ ነው ።
በዓለም ላይ እስልምናም ፣ ካቶሊክም ሆነ ኘሮቴስታንት ሃይማኖቶች የተስፋፉት በግድ በጦርነት ነው ። ይህ አሌ የማይባል ሃቅ ነው ።አስፈላጊም ከሆነ በበቂ መረጃ መናገር ይቻላል ። በተለይ አውሮፓውያኖች ቅኝ ግዛትን ሲያስፋፉ በሚሽነሪዎቻቸው አማካኝነት ጦርነት ኃጢአት እንደሆነና ቀኝህን ሲመታህ ግራህን ስጠው የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ለራሳቸው በሚጠቅም መንገድ በማስተማር በተለይ አፍሪካውያን እራሳቸውን ከወራሪዎች እንዳይከላከሉ ሽባ ለማድረግ የተጠቀሙት ዘዴ ነው ። በጣም የሚገርመው እነሱ ማለትም ወንጌል ሰባኪዎቹ አውሮፓውያኖች ግን ዘመናዊ የጦር መሳሪያ እያመረቱ የሌላን አገር ይወራሉ ። ይህ ተጽእኖ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶም ላይ በስፋት ይታያል ።
አባቶቻችን አትግደል የሚለውን ታቦት ተሸክመው እየጾሙ የተዋጉት ራስን የመከላከል ጦርነት ኃጢአት ሳይሆን ጽድቅ እንደሆነ ስለተረዱ ነው ። ያን ጊዜ ባይዋጉ ኖሮ የአሁኗን የብሔረሰብ ኢትዮጵያን ማግኘት አይቻልም ነበር ።
እራስን ከማንኛውም ውጫዊ አካል ተከላክሎ ትውልድን በነጻነት ማስቀጠል ለሰው ልጆች አርነት ዘብ መቆም በተፈጥሮም ሕግ ፣ በዓለም ዓቀፍ ድንጋጌዎችም ሆነ በመጽሐፍ ቅዱስ ኃጢአት አይደለም ። አንዳንድ የውጭ ጠላቶች የአስተሳሰብ ሰለባ የሆኑ ሰዎች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እራሷን የመከላከል መብት እንደሌላት ሲጽፉ ይታያሉ ። ይህ ኢትዮጵያን የማፍረስ ድብቅ አጀንዳ ሴራ ነው ።
በርካታ ያልተጠቀሱ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች እንዳሉ ልብ ይበሉ ።
Blogger Comment
Facebook Comment