በሀገራችን የመስከረምና የጥቅምት ወራት የአበባ ወራት /ዘመነ ጽጌ/ ይባላል፡፡ ይህም ወቅት ተራሮችና ሜዳዎች በአበባ የሚያጌጡበትና ለዓይን ማራኪ የሚሆኑበት ጊዜ ነው፡፡ ማኅሌተ ጽጌ ማለት ማኅሌት የሚለው ቃል የግእዝ ቃል ሲሆን ትርጉሙም ምስጋና ማለት ነው፡፡ ጽጌ ማለት እንደሱ የግእዝ ቃል ሲሆን ትርጉሙ አበባ የፍሬ ምልክት ማለት ነው፡፡ ማኅሌተ ጽጌ ተብሎ በአንድነት ሲነገር ሲተረጎም ደግሞ የአበባ ምስጋና ማለት ነው፡፡ ይህም ድንግል ማርያም የማኅፀኗ ፍሬ ኢየሱስ ክርስቶስ በጎ መዓዛ ባላቸው አበባዎችና ፍሬዎች እየተመሰሉ የሚመሰገኑበት ምስጋና ማለት ነው፡፡
በቤተክርስቲያናችን ዘመነ ጽጌ ከመስከረም 26 - ህዳር 5 ቀን በማኅሌት በየሳምንቱ እሑድ እሑድ (በተለምዶው ቅዳሜ ሌሊት በሚባለው) በስብሐተ ነግሕ /መኀልየ ሰሎሞን በመቆም/ በማኅሌተ ጽጌ በዘወትርም ጸሎትና ስብሐተ እግዚአብሔር ታከብራለች፡፡
አባ ጽጌ ድንግል ማኅሌተ ጽጌ የተባለውን ድርሰት ደርሰዋል፡፡ የተወለዱትም በሰሜን ሸዋ በይፋት አውራጃ ውስጥ ሲሆን መጀመሪያ ኢአማኒ /ያለመነና ያልተጠመቀ/ ነበር፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን ይህ ሰው በወጣትነት እድሜው አውሬ ለማደን ወደ ጫካ ሄደ በጫካ ውስጥም ፊቷ በጽጌረዳ አበባ የተከበበና ያጌጠ እጅግም ደስ የምታሰኝ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሥዕል ዓይቶ በሥዕሏ ውበት እየተደነቀ ሳለ ጓደኛው መጥቶ ምን እየፈለክ ነው? ይህ እኮ የክርስቲያኖች ሥዕል ነው በማለት በያዘው በትር ሥዕሏን ሲመታት ወዲያው ተቀስፎ ሞተ፡፡ ከዚህ በኋላ ክንፎቹ በጽጌረዳ አበባ ያጌጡ መልአኩ ቅዱስ ሩፋኤል በነጭ ወፍ ተመስሎ ወደ እርሱ መጥቶ ኣንድ ቀይ መነኩሴ እስከሚመጣ ድረስ ይህችን ሥዕል ጠብቃት ብሎ ተሰወረ፡፡
ኢትዮጵያዊው ጻድቅ መነኩሴ አቡነ ዜና ማርቆስ በይፋት አውራጃ በነቢዩ ኢሳይያስ ትንቢት ምዕ፲፩÷፩ “ትውፅእ በትር እምሥርወ እሴይ ወየዐርግ ጽጌ እምኔሃ ” የሚለውን በግእዝ ቋንቋ ሲያነብ በሰማ ጊዜ ኣባቶቼ ኣይሁድ የነቢያት ትንቢት ንባቡን ኣስተምረውኛል፥ አውቀዋለሁ ትርጉሙ ግን ኣላውቀውምና ተርጉምልኝ አለው፡፡
አቡነ ዜና ማርቆስም ሲተረጉምለት እንዲህ አለ "ትወፅእ በትር እምሥርወ እሴይ" የሚለው ንባብ ከእሴይ ነገድ የሕይወት በትር የሆነች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ትወለዳለች ማለት ነው፡፡ "ወይወርድ! ጽጌ እምኔሃ" የሚለው ንባብ ደግሞ እመቤታችን ተወልዳ ከእርሷም ጌታ በድንግልና ይወለዳል፡፡ ከጌታም ክብር ይገኛል ማለት ነው፡፡ ይህም ጌታ ተወልዶ ትንቢቱ በእውነት ተፈጽሟል ብሎ ተረጎመለት፡፡ ( ት ኢሳ፯÷፲፬ ማቴ፲፰፡፳፬ )
ይህ ሰው በዚህ ትርጉም ደስ ተሰኝቶ ኣባት የኢሳይያስን ትንቢት በመልካም ሁኔታ ተረጎምከው መልካም ነገር ተናገርክ አለውና ሥዕሏ ወዳለችበት ቦታ ወስዶ ታሪኩ ላይ እንደተገለጸው በጫካ ውስጥ ያያትን ሥዕል ጓደኛው በያዘው በትር ሲመታት ወዲያው እንደተቀሰፈና ክንፎቹ በጽጌረዳ አበባ ያጌጡ እንደ ነጭ ወፍ የሆኑ (ቅዱስ ሩፋኤል) ወደ እርሱ መጥቶ ቀይ መነኩሴ እስከሚመጣ ድረስ ይህችን ሥዕል ጠብቃት ብሎ በሰው ኣነጋገር ያነጋገረውን ሁሉ ነገረው፡፡
አቡነ ዜና ማርቆስ የተደረገውን ሰምቶ እጅግ ደስ ኣለውና በል በመጀመሪያ እመቤታችን በድንግልና በወለደችው በኣብ የባሕርይ ልጅ በኢየሱስ ክርስቶስ እመን ይህችን ሥዕል ያስገኘው ሰማይና ምድር በውስጣቸው ያለውን ሁሉ የፈጠረ እርሱ እንደሆነ እወቅ ኣለውና በኣብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ኣጥምቆ ጽጌ ብርሃን /ጽጌ ድንግል/ ብሎ ሰየመው፡፡
ማኅሌተ ጽጌን በግጥም /ቅኔ/ ስንኝ በ5 በ5 የተደረሰ ድንቅ ኢትዮጵያዊ ድርሰት ነው፡፡ ይህ ድርሰት በቤተክርስቲያን አገልግሎት የሚውለው በዘመነ ጽጌ እሑድ እሑድ (በተለምዶ ቅዳሜ ሌሊት በሚባለው) በሚቆመው ማኅሌት ነው፡፡ በዚህ ዕለት ሙሉ ድርሰቱ በዜማ በጽናጽልና ከበሮ የሚዘመር ሲሆን በዘወትርና በዓመት በዓላትም በሚቆም ማኅሌት በዓሉን የሚመለከተው ክፍል እያንዳንዱ እየወጣ በዜማና በጽናጽል ይዘምራል፡፡
በዚህ የፅጌ ዘመን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለልብስ ለምን ትጨነቃላችሁ፥ የሜዳ አበቦች እንዴት እንደሚያድጉ ልብ ኣድርጋችሁ ተመልከቱ፡፡ ኣይደክሙም፣ ኣይፈትሉም፣ ነገር ግን እላችኋለሁ ሰሎሞን እንኳ በክብሩ ሁሉ ከእነዚህ እንደ ኣንዱ ኣልለበሰም ብሎ በኣበባ ምሳሌነት የሰው ልጆች ስለ ልብስ እንዳይጨነቁ ኣስተምሯል፡፡ ( ማቴ፭÷፳፰-፴፫ )
ንጉሥ ዳዊትም "ተዘከር እግዚኦ ከመ መሬት ንሕነ ወሰብእሰአ ከመ ሣዕር ወዋዕሊሁ ወከመጽጌ ገዳም ከማሁ ይፈሪ" ኣቤቱ እኛ ኣፈር እንደሆነ ኣስብ ሰውስ ዘመኑ እንደ ሣር ነው እንደ ዱር አበባም እንዲሁም ያብባል ነፋስ በነፈሰበት ጊዜ ያልፋል (መዝ ፻፪፥፲፬-፲፮/) በማለት እንደተናገረው ሣር በቅሎ ኣድጎ ኣብቦ ፀሓይ በወጣ ጊዜ ይደርቅና በሞት ነፋስ ይወሰዳል፡፡
አባ ጽጌ ድንግል የደረሰው ማኅሌተ ጽጌም ምሥጢሩ ከእነዚሁ የቅዱሳት መጻሕፍት መልእክታት ጋር ተቀራራቢ ነው፡፡ የማኅሌተ ጽጌ ብዛቱ 150 ነው፡፡ ጽጌ አስተርአየ ሠረጸ አምኣጽአሙ አበባ ከአጥንቱ ወጥቶ ታየ ብሎ ይጀምራል፡፡ አጥንት ያለው እንጨቱን ነው፡፡ ዕፅ እመቤታችን አበባው ልጅዋ ኢየሱስ ነው በማኅሌተ ጽጌ አበባ ጌታ ሲሆን እመቤታችን ዕፅ ትባላለች ፍሬ ጌታ ሲሆን እመቤታችን ኣበባ ትባላለች፡፡
"እንዘ ተሐቅፊዮ ለሕፃንኪ ጽጌ ጸዐዳ ወቀይሕ አመ ቤተመቅደስ ቦእኪ በዕለተ ተዓምር ወንጽሕ ንዒ ርግብየ ትናዝዝኒ እምላሕ ወንዒ ሠናይትየ ምስለ ገብርኤል ፍሡሕ ወሚካኤል ከማኪ ርኅሩኅ፡
ነጭም ቀይም አበባ የተባለ ልጅሽን እያቀፍሽው በተዓምርና በንጽሕና ቀን ወደ ቤተመቅደስ በገባሽ ጊዜ ርግቤ ድንግል ማርያም ሆይ ከልቅሶ ከሐዘን ታረጋጊኝ ዘንድ ነይ፤ መልካማዬ ከደስተኛው ገብርኤልና እንዳንቺ ርኅሩኅ ከሆነው ከሚካኤል ጋር ነይ"
አባ ጽጌ ድንግል
"ጊዜ ገሚድ በጽሐ ቃለ ማዕነቅ ተሰምዓ በምድርነ፤ ተመየጢ ተመየጢ ወንርዓይ ብኪ ሰላመ፤ እንዘ ተሐቅፊዮ ለሕፃንኪ፤ ክበበ ጌራ ወርቅ ጽሩይ በዕንቈ ባሕርይ ዘየኀቱ፤ አክሊለ ጽጌ ማርያም፤ ንዒ ርግብየ ወንዒ ሠናይትየ፤ እንተ ሐዋርያት ይሴብሑኪ መላእክት ይትለአኩኪ፤ ንዒ እምሊባኖስ ሥነ ሕይወት፤ ቡራኬሁ ለሴም፤ ተናግዶቱ ለአብርሃም መዓዛሁ ለይስሐቅ ወሰዋስዊሁ ለያዕቆብ ወናዛዚቱ ለዮሴፍ …"
"… በአበባው ወቅት መሆን የሚገባው ነገር ሁሉ ደረሰ፡፡ የአዕዋፍ ውዳሴ ቃልም በምድራችን ተሰማ፡፡ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ኾይ! በአንቺ ሰላምን ማየት እንችል ዘንድ መመለስን ተመለሺ፡፡ ልጅሽን እንዳቀፍሽ፤ ክበቡ ያማረ ወርቅ እንደ ተጎናጸፍሽ የአበባ አክሊል ማርያም ርግቤ፣ ደጌ ኾይ! ነይ፡፡ ሐዋርያት የሚያመሰግኑሽ፤ መላእክት የሚላላኩሽ፤ የሕይወት መሠረት ከሊባኖስ ነይ፡፡ የሴም በረከቱ፤ የአብርሃም መስተንግዶው፤ የይስሐቅ ሽቶው፤ የያዕቆብ መሰላሉ፤ የዮሴፍ አጽናኙ …"
የማኅሌተ ጽጌ በረከት በሁላችን ላይ ይደርብን። አሜን!!
መስከረም ፳፬ / ፳፻፲፰ ዓ.ም.
መልካም ወርሃ-ጽጌ!!
Blogger Comment
Facebook Comment