ኢትዮጵያ "አቢሲኒያ" የሚባል ስያሜ ኖሯት አያውቅም


ኢትዮጵያውያን "አቢሲኒያ" በሚባለው ቃል መቼ ነው የተጠሩት? አቢሲኒያ የኢትዮጵያ የጥንት ስም ነው የሚባለው ተረት ተረት ምንጩ ከየት ነው? ለማንኛውም ኢትዮጵያ የምንለው ስያሜያችን ጥንታዊና እጅግ ሰፊ ቦታን የሚወክል ነበር። በአክሱም ዘመነ መንግስት ጊዜ ኢትዮጵያ የሚለው ቃል የዛሬዋን ኢትዮጵያ ከጎረቤቶቿ ከእነ ሱዳን ጭምር በመለየት የሚወክላት ስያሜ መሆኑን የአክሱሙ የመጨረሻ ንጉሥ በ976 ዓ.ም ጊዮርጊስ ለተባለው ለኑብያው ንጉሥ በጻፈው ደብዳቤ ላይ "ድልነዓድ ንጉሠ ኢትዮጵያ" ብሏል፤ ይኼ ማስረጃ ስለተገኘለት ነው እንጂ ከዚያ በፊትም መባሉ አይቀርም።

በአክሱም ጊዜም ሆነ እስካሁን ድረስ የእኛ ነገሥታቶቹ አገራቸውን የሚጠሩት ኢትዮጵያ የሚለውን ስያሜዋን በመጠቀም ነው። በእርግጥ ከአክሱም ዘመን በፊት የነበረችው ኢትዮጵያ ሱዳንና ኤርትራን ጨምሮ ደቡባዊ የግብጽና የአፍሪካ ቀንድ ግዛትንም የሚያካትት ነበረ። በአክሱም ዘመን የነበረችው ኢትዮጵያ ሱዳንን የምትጨምር እንዳልሆነችና በደቡብ ግዛት መዳረሻዋና ወሰኗ ደግሞ የአዛኒያ መንግስት ጋር እንደ ነበር የተገለጸበት ነገር አለ (ላጲሶ ማስረጃ አጣቅሶ እንደዚያ ጽፏል)። የአዛኒያ መንግስት ማዕከሉ የዛሬዋ ታንዛኒያ አካባቢ ነው። 

ኢትዮጵያን ከአክሱም ዘመነ መንግስት በፊት በ25ኛው የግብጽ ሥርወ መንግስት በፒያንኪ ዘመን ካየናት እጅግ ሰፊ አገር ነበረች። በአክሱም ዘመነ መንግስት ጊዜ ደግሞ ሱዳንን ቀንሳለች። በእነ ዓጼ ቴድሮስና ዓጼ ዮሐንስ ዘመን ደቡብን ክፍል ቀንሳለች፤ በዳግማዊ ዓጼ ምኒልክና ኃይለ ሥላሴ ጊዜ ደግሞ የአሁኑን ቅርጿን ይዛለች። ከደርግ ውድቀት በኋላ ደግሞ ኤርትራንም ቀንሳ ኢትዮጲያ እየተባለች አለች። 

የጥንቷን "ኢትዮጵያ" የሚለውን ስያሜ በመውረስ ከ2500 ዓመታት በላይ እስካሁን እየተጠቀመች የቀጠለችው የአሁኗ "ኢትዮጵያ" ናት፤ ሌላ ሀገር የለም። በዓጼ ዘረያ ዕቆብም፣ በዓጼ አምደ ጽዮንም፣ በዓጼ ልብነ ድንግልም ሆነ በዓጼ ቴድሮስና በዓጼ ፋሲል አልያም በራስ ቢትወደድ አሊ ጊዜ ስማችን ኢትዮጵያ ነበር።  

ቤተ መንግስቱ ከአክሱም ወደ ላስታ ከዚያም ወደ ኃይቅና አካባቢው ከዚያም ወደ ሸዋ ቀጥሎ ወደ ጎንደር ከዚያም እንደገና ወደ ሸዋ ሲዘዋወር የኢትዮጵያ ስም ኢትዮጵያ እንጂ አብሲኒያ አልነበረም። የነገሥታቱ ማህተም በራሱ "የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግስት" የሚል ነበር። አንድም የኢትዮጲያ ንጉሠ ነገሥት ራሱን "የአብሲኒያ ንጉሠ ነገሥት" ነኝ ብሎ አያውቅም። እንዲያውም ከዳግማዊ ዓጼ ምኒልክ በፊት የነበሩት ነገሥታት "አቢሲኒያ" የሚለውን ቃል ከነመፈጠሩም አያውቁትም።

ሌላው ቀርቶ በ16ኛው ክፍለ ዘመን የመጣው አልቫሬዝ አቢሲኒያ አላለንም፤ እሱ የጠራት "የቄሱ ዮሐንስ" አገር በማለት ነበር። ይሁንና ከዚያ በኋላ የመጡ አውሮፓውያን፤  በተለይ ከ18ኛው ክፍለ ዘመን ወዲህ ወደ አገራችን የገቡት አቢሲኒያ እያሉ ይጠሩን ነበር። አውሮፓውያን እንደዚያ ቢሉም  የነገሥታቱ ዜና መዋዕሎች ኢትዮጵያ ከማለት በቀር ሌላ ስያሜ አያውቁትም። ይኼ አቢሲኒያ የሚሉት ቃል የእኛ ሳይሆን የፈረንጆች አጠራር ለመሆኑ የሚያስረዳችሁ በፈረንጅ መዛግብት እንጂ በእኛ በአገሬወቹ አለመኖሩ ሊታወቅ ይገባል።

ይሁንና ኢትዮጵያ በ1920 የሊግኦፍኔሽን መስራችና አባል ስትሆን ፈረንጆቹ የሰጧት ስያሜ የለመዱትን "አቢሲኒያ" ሲሆን፤ ንጉሠ ነገሥቱ ግን ራሳቸውን የሚጠሩት ንጉሠ ነገስት ዘኢትዮጵያ እያሉ ነበር። ለነገሩ የሊግኦፍኔሽኑ ስያሜም ብዙም ሳይቆይ ተቀይሯል። በተለምዶ ብዙ ሰዎች አቢሲኒያ ማለት ሀበሻ ለማለት ነው ይላሉ። ሀበሻ ለማለት ቃሉን ወደ አቢሲኒያ መቀየር ለምን አስፈለገ? ፈረንጆቹ "ሀበሻ" ለማለት ምላሳቸው አይሰራ ይሆን? ወይስ ሆሂያቶቹ በእንግሊዝኛ መዝገበ ቃላት ስለሌሉ ነው? 

ምናልባት ግን Abyssinia የሚለው ቃል Abyss ከሚለው የእንግሊዘኛ ቃል ሳይመጣ አይቀርም😊 ትርጉሙም ገደል ማለት ነው። አቢሲኒያ ማለት ሀበሻ ማለት ነው የሚለውን አባባል ግን በዘልማድ ሳይፈተሹ ዝምብለን ስንቀባበልቸው ከነበሩ ተረት ተረቶች መካከል አንዱ ለመሆኑ ለመረዳት አይከብድም።  ያው ፈረንጆቹ ድሮ በ16ኛው ክፍለ ዘመን ወደ አገራችን በእግራቸው ሲመጡ ብዙ ገደላ ገደል ስላጋጠማቸው Abyss-inia ያሉን ይመስለኛል። አገሬዎቹ ግን እንደዚያ መባላቸውን ያወቁት በ20ኛው ክፍለ ዘመን መግቢያ ላይ ነው።

ለማንኛውም አቢሲኒያ የኢትዮጵያ የጥንት ስም አልነበረም፤ ሆኖም አያውቅም። ይሁንና አውሮፓውያን ባንክ ሲከፍቱልን "ባንክ ኦፍ አቢሲኒያ" አሉት። የኛወቹ ሰወች ደግሞ አቢሲኒያ ሲሉ የሰለጠኑ መስሏቸው ለልጆቻቸው፣ ለባንክ፣ ለንግድ ድርጅት ወዘተ ስያሜ ሲሰጡ ኖረዋል። ነገር ግን ምንም የሚያገናኘው ነገር የለም!! በዚህ በኩል ኩሽ ካልተባልን በዚያኛው በኩል አቢሲኒያ ካላልናችሁ ይሉናል። እኛ ግን የሆነውን እናውቃለን!! የኢትዮጵያ የጥንት ስም አቢሲኒያ ነው የሚል ተረት ተረት አውሪ ካለ ማስረጃውን ወዲህ ይበል!!

ሻሎም።
Share on Google Plus

ስለ የተለጠፈበት ቀን

    Blogger Comment
    Facebook Comment