የእመቤታችንና የጌታችን ስደት
እንኳን ለወርኃ ጽጌ አደረሳችሁ፡፡ ወርኃ ጽጌ ማለት ከመስከረም 26 እስከ ህዳር 6 ያለው ወቅት ሲሆን በዚህ ጊዜ በቤተክርስቲያን በማቴ. 2፡13-15፣ በዮሐንስ ራዕይ 12፡1-18፣ እንዲሁም በልዩ ልዩ ቅዱሳት መጻሕፍት የተገለጠው የስደት ወራት የሚታሰብበት ነው፡፡ በዚህ ወቅት የሰማይና የምድር ንጉሥ ኢየሱስ ክርስቶስ በእናቱ በድንግል ማርያም እቅፍ ከዮሴፍና ከሰሎሜ ጋር በመከራ፣ በረሃብ ለ3 ዓመት ከ6 ወር መሰደዳቸውን እናስባለን፡፡ ጌታችን አምላክ ሲሆን በፈቃዱ የተሰደደው ከገነት በኃጢአቱ የተሰደደ የአዳምና የእኛን የአዳም ልጆች የኃጢአት ስደት ሊክስልን (ቤዛ ሊሆነን ነው)፡፡ እመቤታችንም የአምላክ እናት ስትሆን የስደትን መከራ በመቀበሏ ስደትና መከራ ለክርስቲያኖች ክብር እንጂ ውርደት አለመሆኑን እንድንገነዘብ ያደርገናል፡፡ ከእመቤታችን ጀምሮ እግዚአብሔር ለወደዳቸው ቅዱሳን የሰጠው ታላቅ ጸጋ ስለ ጽድቅ፣ ስለ እውነት፣ ስለ ሃይማኖት መሰደድን ነውና፡፡
ለዚያ ነው የተናገረውን የሚፈጽም ቤዛችን፣ አርአያችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስደትን ባርኮ ባስተማረበት የአንቀጸ ብጹዓን ትምህርቱ “ስለ ጽድቅ የሚሰደዱ ብፁዓን ናቸው፤ መንግስተ ሰማያት የእነርሱ ናትና፡፡” (ማቴ• 5:10) ያለው፡፡ ስለ ጽድቅ መሰደድ ማለት ከሀገር ሀገር መሰደድ ብቻ ሳይሆን በሕይወታችንና በኑሯችን ሁሉ የእውነት ምስክሮች ሆነን መኖር ማለት ነው፡፡ ስለ እውነተኝነታችን፣ ሃይማኖታችንን ስለመጠበቃችን ከከሀድያን፣ ከመናፍቃን እንዲሁም ከሌሎች በሀሰት መነቀፍ፣ መሰደብ፣ መዋረድ ቢመጣብን ደስ ሊለን እንጂ ልንከፋ አይገባም፡፡ የክብር ባለቤት፣ ስደትን የባረከ ኢየሱስ ክርስቶስ “ስለ እኔም እየዋሹ ክፉውን ሁሉ በሚናገሩባችሁ ጊዜ ብፁዓን ናችሁ፡፡ ደስ ይበላችሁ፤ ሐሤትንም አድርጉ፤ ዋጋችሁ በሰማያት ብዙ ነውና፤ ከእናንተ አስቀድሞ የነበሩ ነቢያትንም እንዲሁ አሳደዋቸው ነበርና” (ማቴ. 5፡11-12) በማለት የሰጠንን ቃልኪዳን በማሰብ ልንጸና ይገባል፡፡
በኃጢአታችን ምክንያት የሚደርስብንን ነቀፋና ስድብ ግን በንስሃ ማስወገድ አለብን እንጂ የኃጢአትን ዋጋ ለጽድቅ የተከፈለ መስዋእትነት አስመስለን ራሳችንን በሀሰት ለማጽደቅ ልንሞክር አይገባም፡፡ “አትሳቱ እግዚአብሔር አይዘበትበትም። ሰው ሁሉ የዘራውን ያንኑ ደግሞ ያጭዳልና” እንደተባለ (ገላትያ 6:7)፡፡ ስለሆነም የእመቤታችንን ስደቷን፣ መከራዋን በምናስብበት በዚህ ወራት እኛም ስለጽድቅ በመነቀፍ የጽድቅን ዋጋ እንድንቀበል በኃጢአታችን ምክንያት የሚመጣብንን ፈተናም በግብዝነት ራሳችንን ጻድቅ ለማስመሰል ከመጠቀም ተቆጥበን በንስሐ ታድሰን የመንግስተ እግዚአብሔር ወራሾች እንድንሆን ያስፈልጋል፡፡
ስለ ጽድቅ የተሰደዱ የክርስቶስ ምስክሮች
“ስለ ጽድቅ የሚሰደዱ ብፁዓን ናቸው፤ መንግስተ ሰማያት የእነርሱ ናትና”(ማቴ. 5፡10) የሕይወታቸው መመመሪያ በማድረግ አማናዊ ጽድቅ ስለሆነ ስለክርስቶስ ፍቅር ምድራዊ መከራን በቅንነት በመቀበል ሰማያዊ ዋጋ ካገኙ አዕላፋት ቅዱሳን መካከል በዘመነ ጽጌ መካከል ጥቅምት 14 ዓመታዊ መታሰቢያ በዓላቸውን የምናከብርላቸውን ሁለት ዐበይት ቅዱሳን ታሪክ ስለ ጽድቅ የተሰደዱ/የሚሰደዱ ክርስቶሳውያን ማሳያ አድርገን እንመልከት። እነርሱም አቡነ አረጋዊ እና ጻድቁ ገብረክርስቶስ ናቸው።
አባታችን አቡነ አረጋዊ በሀገራችን ኢትዮጵያ የወንጌልን ብርሃን ካበሩት ዘጠኙ ቅዱሳን አንዱ ናቸው፡፡ ትውልዳቸው ሮም ሲሆን ከኬልቄዶን ጉባኤ (451 ዓ.ም.) በኋላ የሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ከቀደሙ አባቶች ርትዕት ሃይማኖት በተለየ መልኩ የንስጥሮስን ክልኤ ባህርይ (ሁለት ባሕርይ) አስተምህሮ በመከተል የተዋሕዶን አስተምህሮ በሚከተሉ አባቶች ላይ በነገስታት ተደግፋ መከራ ስታጸና ሃይማኖታቸውን ጠብቀው ስለጽድቅ ሀገር አቋርጠው ተሰደዱ፡፡ በሀገራችን በኢትዮጵያ ገዳማትን በማስፋፋት፣ ሥርዓተ ምንኩስናን በማጽናት የጠበቋትን ርትዕት ሃይማኖት አስፋፍተዋል፡፡ ራሳቸውን ለእግዚአብሔር ስላስገዙ ጌታ እግዚአብሔር ስጋውያን ፍጥረታት እንዲገዙላቸው በሰጣቸው ጸጋ ክፉ ዘንዶ እንኳ ታዞላቸው የደብረ ዳሞን ተራራ ለመውጣት ተጠቅመውበታል፡፡ በጸሎታቸው፣ በመንፈሳዊ ተጋድሏቸው እግዚአብሔርን ደስ ስላሰኙት ስለ ክርስቶስ ስም መከራን ሳይሰቀቁ ተቀብለዋልና ሞተ ሥጋ ሳያገኛቸው ከአምስቱ ዓለማተ መሬት አንዷ ወደሆነችው ወደ ብሔረ ህያዋን እንደ ኄኖክና እንደ ኤልያስ ተነጥቀዋል፡፡ ስለ ጽድቅ፣ ስለ ክርስቶስ ተሰድደዋልና የመንግስተ ሰማያት አረቦን (መያዣ) ወደሆነች ብሔረ ህያዋን ለመግባት ክብር በቁ፡፡ እኛም የስደት ነገር ጎልቶ በሚታሰብበት በወርኃ ጽጌ፣ በየዓመቱ ጥቅምት 14 ወደ ብሔረ ህያዋን መነጠቃቸውን እያሰብን እንዘክራቸዋለን፡፡
ጻድቁ ገብረክርስቶስ የቁስጠንጥንያ ንጉስ የነበረው ቴዎዶስዮስ ልጅ ነው፡፡ ሚስት አግብቶ የአባቱን ንግስና ወርሶ እንዲኖር በሰርግ ዳሩት፡፡ እርሱ ግን ምድራዊ ደስታን የናቀ ነበር፣ ስለ ክርስቶስ በፈቃዱ መነቀፍንም ይፈልግ ነበር፡፡ ከጫጉላ ቤትም የተዳረችለትን ሚስቱን በግብር ሳይደርስባት ህገ እግዚአብሔርን እየጠበቀች እንድትኖር አደራ ብሏት ወደ ምናኔ ወጣ፡፡ በአንዲት ቤተክርስቲያንም 15 ዓመት በመንፈሳዊ ተግባር ተጠምዶ ኖረ፡፡ በዚህ ሁሉ ዘመን ራሱን ዝቅ አድርጎ እንደ ኃጢአተኛ ከቤተክርስቲያኑ ውጭ ይኖር ነበር፡፡ ከ15 ዓመት በኋላ እመቤታችን ቤተክርስቲያኑን ለሚያስተዳድረው ቄስ ተገልጣ የገብረክርስቶስን ማንነት አሳወቀችው፤ አክብሮ ወደ ቤተክርስቲያን እንዲያስገባውም ነገረችው፡፡ ይህን በራዕይ የተረዳው ጻድቅ ገብረክርስቶስ ግን ክብሩ በመገለጡ አዘነ፡፡ እመቤታችንን በጸሎት ለምኖ ክብሩ ወደማይታወቅበት ቦታ በመርከብ ተሰደደ፡፡
የጌታ ፈቃድ ሆኖ ወደ አባቱ ሀገር ደረሰ፡፡ በአባቱ ቤት ደጃፍ ከድሆች ጋር ለ15 ዓመት ውሾች እያሰቃዩት ኖረ፡፡ በአባቱ አገልጋዮች ያለበደሉ መከራ ሲጸናበት ምንም ምን የበቀል ልብ አልነበረውም፡፡ ጥቅምት 14 በሞተ ስጋ ሲለይ እናትና አባቱ በበራቸው የነበረው ደሃ ልጃቸው መሆኑን እግዚአብሔር በተዓምራት ገለጸላቸው፡፡ ጻድቅ ገብረ ክርስቶስም ገድሉን ጽፎ በክርታስ ይዞ ተገኘ፡፡ ስለ ጽድቅ የተሰደደው ጻድቅ ገብረክርስቶስ ነፍሱ በገነት አረፈች፤ ከጌታ በተቀበለው ቃልኪዳንም በምግባር የደከምን ኃጢአተኛ ልጆቹን መታሰቢያውን እያደረግን የመንግስተ ሰማያት ወራሾች እንድንሆን ይረዳናል፡፡ እኛም ክርስቶሳውያን መሆናችን እንዲገለጥ እንደነዚህ ቅዱሳን በአቅማችን ስለጽድቅ ተሰድደን (ተነቅፈን) የመንግስተ እግዚአብሔር ባለቤት እንሆን ዘንድ በመንፈሳዊ ሕይወታችን ልንጸናና ልንተጋ ይገባል፡፡
ጽድቅን የሚያሳድዱ አመጸኞች
ስለ ጽድቅ መሰደድ የክርስቶስ ወገን፣ የእመቤታችን ወዳጅ የሚያደርግ ሲሆን ጽድቅን ማሳደድ ደግሞ በአንፃሩ የሄሮድስ ክፋት ተካፋይ ያደርጋል። ጽድቅን ማሳደድ ማለት ከሀሰት ወግኖ እውነትን መግፋት፣ በጽድቅ አገልጋዮች ላይ መከራን ማጽናት፣ ራስንም ከጽድቅ ሥራ ከልክሎ የኃጢአት አገልጋይ መሆን ማለት ነው። ለዚህም በወርኃ ጽጌ ታሪካቸው የሚተረክላቸውን ሦስት አካላት መነሻ እናደርጋለን፡፡ እነርሱም ሄሮድስ፣ የሄሮድስ ወታደሮችና ኮቲባና ቤተሰቦቿ ናቸው።
በመጀመሪያ ከክፉ ታሪኩ የምንማርበት የጽድቅ አሳዳጅ የጽድቅ መሠረት ኢየሱስ ክርስቶስን ከተወደደች እናቱ ጋር በግፍ ያሳደደ ሄሮድስ ነው። በማቴ. 2፡3-13 በተጻፈው መሰረት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመወለዱ ሰብአ ሰገልም “የተወለደው የአይሁድ ንጉስ ወዴት ነው?” ብለው ሲፈልጉት ስላየ ርጉም ሄሮድስ ደነገጠ፡፡ ሄሮድስ ርጉም ነውና የሚያስጨንቀው ጽድቅና እውነት ሳይሆን ምድራዊ ክብሩና አለቅነቱ ነው፡፡ ሌላ ንጉስ መጥቶ የሚገለብጠው ስለመሰለው “ሳያድግ ልግደለው” ብሎ ጌታችንን አሳደደው፡፡ እርሱን ያገኘ መስሎትም እልፍ ሕፃናትን አስገደለ፡፡ ሄሮድስ ጽድቅን ለክብሩ ብሎ በማሳደዱ አልተጠቀመም፡፡ ይልቁንም አሟሟቱ እንኳ ከፍቶ ሰውነቱ ተልቶ ሞተ፡፡ በሲዖል፣ ኋላም በገሀነመ እሳትም ከዚህ የባሰ ፍርድ ይጠብቀዋል፡፡ እውነትን በሀሰት አሳድዷልና ነፍሱ ትቅበዘበዛለች፡፡ ሄሮድስ ለምድራዊ ክብር ሲሉ እውነተኞችን የሚያሳድዱ ምድራውያን ባለስልጣናትን ይመስላል፡፡ ከዚያም ባሻገር ለሰማያዊ ክብር በእግዚአብሔር ህዝብ ላይ ለአገልግሎት ተሹመው ልብስና ሥም ብቻ ለሚከልለው መንፈሳዊነት ለጎደለው ክብራቸው ሲሉ የጽድቅ፣ የክርስቶስ መልእክተኞች የሆኑ ቅዱሳንንና እውነተኞች ምዕመናንን ያለእውነት በሀሰት ከቤተክርስቲያን የሚያርቁ የዘመናችን የጽድቅ ጠላቶችም ተረፈ ሄሮድሳውያን ናቸው፤ ፍጻሜአቸውም ከሄሮድስ የከፋ ይሆናል፡፡
በሁለተኛ ደረጃ መማሪያ የሚሆኑን የሄሮድስ ወታደሮች ናቸው፡፡ የሄሮድስ ወታደሮች እውነትን ከሀሰት መለየት የማይችሉ ለህሊናቸው ሳይሆን ለቀጠራቸው ለሄሮድስ የሚታዘዙ የእውነት ጠላቶች ናቸው፡፡ እመቤታችን ከጌታ ጋር በተሰደደች ጊዜ በርሃ ለበርሃ እየተከታተሉ መከራ ያጸኑባቸው ነበር፡፡ ይህን የሚያደርጉት እውነት ገብቷቸው ሳይሆን እንደ አምላክ የሚገዙለትን የሄሮድስን የረከሰ ሀሳብ በመሙላት ሹመትና ሽልማት ማግኘት የሚፈልጉ ህሊናቸውን ለጥቅም፣ ወይም ለጊዜያዊ የማስመሰል ክብር ያስገዙ ናቸው፡፡ የአምላክን እናት በበርሃ እያሳደዱ በውኃ ጥም እንድትቀጣ ሲያደርጉ እነርሱም ይጠሙ ነበር፡፡ በተዓምረ ማርያም እንደተመዘገበው ጌታችን በተዓምራት በበርሃው መካከል ለእናቱ፣ ለዮሴፍና ለሰሎሜ ንጹህ ምንጭን አፈለቀላቸው፡፡ ይህች ምንጭ ለተሳዳጆች መልካም መጠጥ ሆነችላቸው፡፡ አሳዳጆቹ ሊጠጧት ሲጠጉ ግን መራራ ትሆንባቸው ነበር፡፡ በሲዖል፣ ኋላም በገሀነመ እሳትም ከዚህ የባሰ ፍርድ ይጠብቃቸዋል፡፡ ለምድራውያን ባለስልጣናት እንዲሁም የእግዚአብሔርን አገልግሎት ለግላዊ ጥቅምና ዝና ለሚያውሉ ምንደኞች ሲሉ እውነተኞችን የሚያሳድዱ የሀሰት መልእክተኞች የሄሮድስን ወታደሮች ይመስላሉ፤ ፍጻሜአቸውም ከሄሮድስ ወታደሮች የከፋ ይሆናል፡፡
በሦስተኛ ደረጃ እመቤታችን ጌታን ይዛ በመከራ ውስጥ ምግብና መጠጥ ስትለምናቸው በማያውቁት በመፍረድ እመቤታችንን “አንቺ መልክሽ ያማረ ነው ፀባይሽ ክፉ ቢሆን ነው እንጂ የተሰደድሽው በነገስታት ቤት ትኖሪ ነበር” ብለው ያሳዘኗት ክብር ይግባውና ፈጣሬ ዓለማት ክርስቶስንም ካዘለችበት አውርደው በጥፊ የመቱት ኮቲባና ቤተሰቦቿም የሚያስተምር ታሪክ አላቸው፡፡ ባላወቁት ፈርደው የተቸገሩትን ገፍተዋልና፣ የግፍ ግፍም ፈጽመዋልና ጌታችን በተዓምራት ወደ ዝንጀሮ እንዲቀየሩ አደረጋቸው፣ የቤታቸው ውሾችም አባረሩዋቸው፡፡ በሲዖል፣ ኋላም በገሀነመ እሳትም ከዚህ የባሰ ፍርድ ይጠብቃቸዋል፡፡ ኮቲባና ቤተሰቦቿ በምድራዊ መከራ ያለበደላቸው የሚሰቃዩ ነዳያንን የሚንቁ የሚገፉ እንዲሁም የጽድቅ አገልጋዮችን ያለስማቸው ስም የሚሰጡ በማያውቁት እየገቡ በችግራቸው ላይ ተጨማሪ ፍዳን የሚያጸኑባቸውን ርህራሄ የሌላቸው ሰዎችን ይመስላሉ፤ ፍጻሜአቸውም ከኮቲባና ቤተሰቦቿ የከፋ ይሆናል፡፡
ክቡራን ክርስቶሳውያን ጌታችንን የሚያስመስለን፣ ከእመቤታችን የስደት በረከት የሚያጋራን፣ የመንግስተ ሰማያት ወራሾች የሚያደርገን ስለ ጽድቅ መሰደድም ሆነ የረከሰ ሄሮድስን የሚያስመስለን፣ ከቅዱሳን በረከት የሚለየን፣ የገሀነም ልጆች የሚያደርገን ጽድቅን ማሳደድ የየዕለት ሕይወታችን አካል መሆናቸውን ማስተዋል ይገባናል። ጌታችን በወንጌል እንዳስተማረን “የእግዚአብሔር መንግስትስ እነኋት፣ በመካከላችሁ ናት።” (ሉቃ• 17:21) ስደት ስለ ጽድቅ መሰደድ በአጠገባችን ያለ እንደሆነው ሁሉ ጽድቅን ማሳደድም በመካከላችን ነው፡፡ ጽድቅን ከሚያሳድዱት ክፉዎች ጋር ሆነን በሲዖል በገሀነመ እሳት እንዳንጣል፣ ስለጽድቅ ከሚሰደዱት ጋር ሆነን የእግዚአብሔር መንግስት ወራሾች እንሆን ዘንድ ማስተዋልንና ጽናትን ገንዘብ ልናደርግ ይገባል፡፡
ስደት ወደ መንግስተ ሰማያት መሸጋገሪያ ነው!
በምድራዊ ኑሮአችን ስለ ጽድቅ እንደ አቅማችን መከራ ብንቀበል ምድራዊ ስደትና መከራ የሚያልቅ፣ የተቆረጠ መሆኑን ቅዱሳት መጻሕፍት ያስረዱናል። የወርኃ ጽጌን ታሪክ አመስጥረው ከጻፉልን ቀደምት አባቶቻችን አንዱ የሰው ልጆችን ሁሉ ወክሎ እመቤታችንን በአደራ እናትነት የተቀበለው (ዮሐ. 19፡26፣ ራእይ 12:1~ፍፃሜ) ፍቁረ እግዚእ ወንጌላዊ ቅዱስ ዮሐንስ አንዱ ነው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ ስለ ሃይማኖት ምስክርነቱ፣ እውነትን ከመናገሩ የተነሳ ምድራውያን ባለስልጣናት ወደ ፍጥሞ ደሴት በግዞት (በስደት) እንዲወሰድና እንዲታሰር አደርገውት ነበር፡፡ ጻድቅና ቅዱስ ዮሐንስ ግን ስደት ወደማታልፍ መንግስተ ሰማያት መሸጋገሪያ እንደሆነ ያውቅ ነበርና በግዞቱ አልተከፋም ነበር፡፡ ይልቁንስ በግዞት በመታሰሩና እንደ ሌሎች ቅዱሳን ሐዋርያት ተዘዋውሮ ወንጌልን ባለማስተማሩ ያዝን ይተክዝ ነበር፡፡ የለመኑትን የማይነሳ ጌታም በራዕይ ሰማያዊ ምሥጢርን ገልጾለት ዮሐንስ ራዕይ የምንለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ጽፏል፡፡ በሥጋ የተሰደደው ስደት ሞት ሳያገኘው ወደ ብሔረ ሕያዋን ከመሄድ አልከለከለውም፡፡ ይልቁንም ወደ መንግስተ ሰማያት መሸጋገሪያ ሆነው እንጂ፡፡
ይህ የከበረ ሐዋርያ ዮሐንስ የእመቤታችንን (እንዲሁም የቤተክርስቲያንን) የስደቷን ርዝመት ነገር በተናገረበት አንቀጽ እነዲህ አለ “ሴቲቱም በዘመኑ ሁሉ አንድ ሺህ ሁለት መቶ ስሳ ቀን በዚያ ትጠበቅ ዘንድ እግዚአብሔር ወደ አዘጋጀላት ቦታ ወደ በረሃ ሸሸች፡፡” (ዮሐ. 12፡6) ይህ 1260 ቀን፣ ወይም 42 ወራት፣ ወይም ሦስት ዓመት ከስድስት ወር የእመቤታችን የስደት ወቅት ርዝማኔ ነው፡፡ መተርጉማነ ሐዲስ አባቶቻችን እንዳስተማሩን እነዚህ የስደት ቀናት በቁጥር ተለይተው መታወቃቸው ስለ ጽድቅ የሚሰደዱ፣ መከራ የሚቀበሉ ቅዱሳን የሚቀበሉት ምድራዊ መከራ የሚያልፍ፣ የሚቆጠር መሆኑን ያሳያል፡፡ በአንጻሩ ስለ ስሙ በመሰደዳቸው፣ መከራ በመቀበላቸው ጌታችን የሚሰጣቸው ሰማያዊ መንግስት ግን የማታልፍ፣ ዘመን የማይቆጠርባት፣ ዘላለማዊት ናት፡፡ የስደቱ ዘመን (42 ወራት) በሌሎች ቅዱሳን ሕይወትም የተፈጸመ ነው፡፡
በኦሪት ዘጸአት የተመዘገበው የእስራኤል ዘሥጋ ስደት 42 ዓመታትን ወስዷል፡፡ ከእስራኤል መካከል እግዚአብሔርን ያስደሰቱት ስደቱ፣ መከራው አልፎላቸው ከነዓን ገብተዋል፡፡ አሳዳጃቸው ፈርኦንና ሰራዊቱ ግን በመቅሰፍት ጠፍተዋል፡፡ በመጽሐፈ ነገስት የተመዘገበው ነቢየ እግዚአብሔር ኤልያስ ስለ ደሃው በመሟገቱ፣ የእግዚአብሔርን ቃል በመናገሩ ኤልዛቤልና አክአብ ያሳደዱት ስደት 42 ወራትን ወስዷል፡፡ ኤልያስ ስደቱ አልፎለት፣ ወደ ብሔረ ሕያዋን መሸጋገሪያ ሆኖት በክብር አረገ፡፡ አሳዳጆቹ ኤልዛቤልና አክአብ ግን ሞተዋል፣ መታሰቢያቸውም ተረስቷል፡፡ በቀጣይ ቀናት በቤተክርስቲያናችን እንደሚመሰከረው እመቤታችን ከተወደደ ልጇ ጋር የተሰደደችው ስደትም ተፈጽሟል፤ ከሄሮድስ ሞት በኋላ ወደ ናዝሬት፣ ወደ ገሊላ ተመልሰዋል፡፡ አሳዳጃቸው ሄሮድስ ግን ክፉ ሞትን ሞቷል፡፡ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች እኛም እያንዳንዳችን የእውነት፣ የእግዚአብሔር ቃል ታማኝ ምስክሮች ልንሆን ይገባል፡፡ የጽድቅ ምስክሮች ከመሆናችን ተነሳ መከራን ስደትን ለመቀበል እንደ ቅዱሳን አባቶቻችን የበቃን የምንሆንበት ጊዜ ከመጣ በደስታ ልንቀበለው ይገባል፡፡ ስደት፣ መከራ ወደ መንግስተ ሰማያት የምንሸጋገርበት ድልድይ እንጂ ተስፋ እንደሌላቸው የምንቅበዘበዝበት ቅጣት አይደለምና፡፡
የእመቤታችን ስደት ማብቃትና ወደ ገሊላ መመለስ
በየዓመቱ ኅዳር 6 በወርኃ ጽጌ ፍጻሜ እመቤታችን ድንግል ማርያም ከተወደደ ልጇ ጋር፣ እንዲሁም ከዮሴፍና ሰሎሜ ጋር በሄሮድስ ምክንያት የደረሰባቸው ስደትና መከራ አልፎ ደብረ ቁስቋም በተባለች ቦታ ያረፉበት ነው፡፡ ወንጌላዊው ቅዱስ ማቴዎስ እንደፃፈልን “ሄሮድስም በሞተ ጊዜ እነሆ የእግዚአብሔር መልአክ በግብፅ ሀገር ለዮሴፍ በሕልም ታየው፡፡ እንዲህ ሲል ‘የሕፃኑን ነፍስ የሚሹ ሙተዋልና ተነሥተህ ሕፃኑንና እናቱን ይዘህ ወደ እስራኤል ሀገር ሂድ’፡፡” (ማቴ. 2፡20) ባለው መሰረት አረጋዊ ዮሴፍ ሰሎሜ እያገዘችው የሚያገለግላትን ቅድስት ድንግል እመቤታችንን ከተወደደ ልጇ ጋር ይዞ ከስደት መመለሳቸውን እናስባለን፡፡
የእመቤታችን (እንዲሁም የቤተክርስቲያን ስደት) ቀኑ በእግዚአብሔር ዘንድ በቁርጥ የታወቀ ነበር፡፡ ይሁንና አንዱ ስደት ሲቆም ሌላው መከተሉ በቅዱሳን ሕይወት ዘንድ የተለመደ ነው፡፡ ስደታቸውም የክብር መሰላል ሆኗቸው ከክብር ወደክብር የሚሸጋገሩበት ነው፡፡ ቅዱሳን በሕይወታቸው አንዱን መከራ (ስደት) በድል ሲወጡ የሚያገኙት የማያልቅ ጸጋ አለ፡፡ ቅዱሳን መላእክትም በቅዱሳን ሰዎች ተጋድሎ ሰይጣን ሲሸነፍ በሰማያት ታላቅ ደስታ ያደርጋሉ፡፡ የክብር ባለቤት የኢየሱስ ክርስቶስ እናቱ ወላዲተ አምላክ ድንግል ማርያም በስደቷ እግዚአብሔርን አላማረረችም፡፡ ስለሆነም ሰይጣንን በትዕግስቷ በጸሎቷ አሸነፈችው፡፡ ልጇ ወዳጇ ኢየሱስ ክርስቶስም የመንግስተ ሰማያት ምሳሌ የሆነች እረፍትን በደብረ ቁስቋም አሳረፋት፡፡ ደብረ ቁስቋም ግን ምሣሌ እንጂ አማናዊ (ሰማያዊ) የእረፍት ቦታ አይደለችም፡፡ ስለሆነም ከደብረ ቁስቋም እረፍት በኋላ እመቤታችን ከአምስቱ ታላላቅ ሀዘኖቿ አራቱን አስተናግዳለች፡፡
ከእመቤታችን ሕይወት የምንማረው ትልቅ ቁም ነገር በክርስትና ሕይወታችን፣ እውነተኞች በመሆናችን ከሚመጣብን መከራ አንዱ ሲያልፍ ራሳችንን ለሌላ መከራ ማዘጋጀት እንጂ አንዲት ፈተና ስላለፍን በትዕቢት ተይዘን ራሳችንን በግብዝነት ማጽደቅ እንደማይገባ ነው፡፡ ያን አድርገን እስከ መጨረሻው ከጸናን ቅዱሳን ሐዋርያት “በብዙ ድካምና መከራ ወደ እግዚአብሔር መንግስት እንገባ ዘንድ ይገባናል” (ሐዋ. 14፡22) በማለት የመከሩንን አስበን የድኅነትን ነገር መቀለጃ ከሚያደርጉ አላዋቂ መናፍቃን የማታለል ትምህርት ርቀን ተስፋ የምናደርጋትን አማናዊት ደብረ ቁስቋም (መካነ እረፍት) ኢየሩሳሌም ሰማያዊትን ሊያወርሰን የታመነ አምላክ አለን፡፡ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ከልጇ ጋር ደረሰባትን የ3 ዓመት ከ6 ወር ስደትና መከራ በትዕግስት በፈጸመች ጊዜ የልዑል እግዚአብሔር ኃይሉ ጥበቃው አልተለያትም ነበር፡፡ በጉዞዋ ሁሉ ይረዷት የነበሩት ቅዱሳን መላእክትም ከበዋት ያመሰግኑ ነበር፡፡ ለዚያ ነው ቤተክርስቲያናችን “መንክረ ግርማ ኃይለልዑል ጸለላ፤ አማን መላእክት ይኬልልዋ (2)” (በሚያስደንቅ ግርማ የልዑል ኃይል ጋረዳት፣ በእውነት መላእክት አመሰገኗት (2) )እያለች በከበረ ዜማ የምታመሰግነው፡፡ ይህ በእመቤታችን ሕይወት የተገለጠ የልዑል እግዚአብሔር ጥበቃ፣ የቅዱሳን መላእክት ረዳትነት በክርስቶስ አምነው ስለ ሥሙ፣ ስለሰጠን ደገኛ ሃይማኖት ብለው መከራ መቀበልን፣ መነቀፍን በደስታ ለሚቀበሉ ሁሉ የተሰጠ ነው፡፡ አምላካችን እግዚአብሔር ጽድቅን ከሚያሳድዱ ሄሮድሳውያን ተለይተን ስለ ጽድቅ ከተሰደዱ/ከሚሰደዱ ክርስቶሳውያን ጋር ተባብረን፣ በጸሎታቸው በቃልኪዳናቸው ተደግፈን በሕይወታችን እንድናስደስተው ቅዱስ ፈቃዱ ይሁንልን፡፡ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም የስደቷ በረከት ከሁላችን ጋር ይሁን፡፡ አሜን፡፡
Blogger Comment
Facebook Comment