ኢትዮጵያ፡ ሥርዓተ ሢመተ ጵጵስናን ስትፋረድ!


በንቡረ-እድ ኤርምያስ ከበደ ወልደኢየሱስ፣ ዘአኵሱም ጽዮን።

እንግዴህ፡ ዛሬ ባሉት ጳጳሳት ተግባር የማልደነቀውና ስለእነርሱም ኾነ፡ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያዊነትን በሚመለከት፡ "እንዲህ ቢኾን፥ እንዲህ ቢደረግ ይሻላል!" የምለው፡ ያለምክንያት አይደለም። እነርሱ፡ ጳጳሳቱ፡ ሥጋ ለባሽ ሰዎች ስለኾኑ፡ ባለማዎቅም፥ በማዎቅም፡ ሊሳሳቱና ሊያጠፉ ይችላሉና፡ "የአገራችን፥ የሃይማኖታችንና የቤተ ክህነታችን ጉዳይ፡ ለእነርሱ ብቻ ሊተው አይገባም! አደገኛ ነው! ስለዚህ፡ ቤተ ሕዝቡ፡ በኢትዮጵያዊነት የቃል ኪዳን ሃይማኖታውያንና መንፈሳውያን ይዞታዎቹ፥ ውርሶቹና ቅርሶቹ ጥበቃ በኩል፡ ታላቅ የኃላፊነት ድርሻ ስላለው፡ ግዳጁን ይፈጽም! አለዚያ፡ እያንዳንዱ የቤተ ሕዝቡ አባል፡ ሴትም ኾነች ወንድ፡ በሕሊናው፥ በአገሩና በእግዚአብሔር ፊት፡ በኃላፊነት መጠየቅ አይቀርምና፡ በዚያን ጊዜ፡ ስለሚሰጠው መልስ፡ እንዳይቸገርና እንዳይጸጸት ከአሁኑ ይጠንቀቅ!" እያልኩ አሳብ የማቀርበውና የማሳስበው እኮ! በማውቀው፥ ባየሁትና በደረሰብኝ እንጂ፡ እንዲያው ዝም ብዬ በመላምት፥ በዳበሳና በስሜት አይደለም።

ጵጵስናን፡ ለመነኰሳት ብቻ ወስኖ የሰጠ ማነው?

ታዲያ ለምንድር ነው፡ በዚህ ግብፃውያን ባሸከሙን ከባድ ቀምበር፡ ራሳችንን ጠፍረን፡ ስንሠቃይ የምንኖረው? ይህ ሥርዓት፡ ከእኒሁ፡ ከባዕዳኑ ግብፃውያን ጨቋኞቻችን ያመጣነው ዕዳ እንጂ፡ ጥንቱንም ቢኾን፡ የእኛ የኢትዮጵያውያን አይደለም። እነርሱም፡ እስከዛሬ ድረስ ሲያደርሱብን የኖሩት አንሶ፡ ይኸው ዛሬም፡ በደሉንና ግፉን፡ በኢየሩሳሌም ይዞታችን ላይ በገሀድ ሲፈጽሙብን እናያለን።

በእኛ፡ በኢትዮጵያውያኑ ጥንታዊ ሥርዓት፡ የሊቀ ካህናትነቱ ሥልጣን የተመሠረተው፡ በኋላ በመጣው፡ በምንኵስና ላይ ሳይኾን፡ ቀደም ብሎ በነበረው፡ በድንግልና፥ በብሕትውናና በጋብቻ ላይ እንደኾነ፡ ሕያው የኾነው ዜና መዋዕላችን ያረጋግጥልናል። ይህም፡ በዘመነ ብሉይ፡ በእነመልከ ጼዴቅ፥ በእነዮቶር፥ በእነሙሴና ሚስቱ ሲጳራ፥ በእነአሮንና በእነንግሥት ማክዳ፥ በዘመነ ሓዲስ ደግሞ፡ የአኵሱሙ ሊቀ ካህናት፥ ንቡረእድና እጨጌ በነበረው፡ በእነእንበረም፥ ከእርሱ በፊትና ከእርሱ በኋላ በተሾሙትም፡ ሊቃነ ካህናት ሕይወት ይታወቃል።

በዘመነ ክርስትና፡ የኋላ ኋላ፡ በ፬ኛው ምዕት ዓመት፡ ወደአገራችን የገባውና ከግብፃውያን ያገኘነው ምንኵስናም፡ እንደጌታ ቃል፡ በየግላቸው ለተመረጡትና ለተጠሩት የሚገባ፡ የቅድስናና የገድል ሕይወት ሲኾን፡ "ዕዳ፥ ቀምበር" ያልኩት፡ ምንኵስናውን ሳይኾን፡ በሰዎች ሥርዓት፡ በእርሱ ላይ ብቻ እንዲመሠረት የተደረገውን፡ የጵጵስናውን ሢመት ነው። ዓቢዩ ጥያቄ፡ "የጵጵስናው ሹመት፡ ለምን፡ ለመነኰሳት ብቻ ይኾናል?" በሚለው ነጥብ ላይ ይመሠረታል። ለዚህም፡ በዋቢነት የሚቀርቡት ማስረጃዎች፡ የራሱ የአምላካችን ቃላት ናቸው።

እግዚአብሔር፡ ጥንት በፍጥረት መጀመሪያ፡ በአዳምና ሔዋን መሥርቶት ያገኘነውና እርሱም እንድንጠብቀው ያዘዘን፥ ኋላም፡ በመጨረሻው ዘመን፡ ሰው ኾኖ፡ ያጸናው፡ የአንድ ወንድንና የአንዲት ሴትን ጋብቻን እንጂ፡ ምንኵስናን አይደለም። ይህንኑም፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፡ ስለጋብቻ አንድነትና ጽናት አብራርቶ ካስተማረ በኋላ፡ ፍቺ እንዳይኖር በማስጠንቀቅ፡ ለተናገረው ቃል፡ ደቀ መዛሙርቱ ሳይቀሩ ተጨንቀው፡ "የባልና ሚስት ሥርዓት እንዲህ ከኾነ፡ መጋባት አይጠቅምም!" ላሉት፡ መልሱን የደመደመው፡ "ይህ ነገር፡ ለተሰጣቸው ነው እንጂ፡ ለኹሉ አይደለም፤ በእናታቸው ማሕፀን፡ ጃንደረቦች ኾነው የተወለዱ አሉ፤ ሰውም የሰለባቸው፡ ጃንደረቦች አሉ፤ ስለመንግሥተ ሰማያትም፡ ራሳቸውን የሰለቡ ጃንደረቦች አሉ፤ ሊቀበለው የሚችል ይቀበለው!" በማለት፡ በሚገባና በሚበቃ ገልጾታል። እንግዴህ፡ "ከእርሱ፡ ከመለኮት ቃል፡ የበለጠ ቃል፥ ከእርሱ፡ ከመለኮት ሥርዓትም የበለጠ፡ ሥርዓት አለ!" ሊል የሚችል ደፋር፡ ይኖራል ብዬ አልገምትም።

ጵጵስናን፡ ለመነኰሳት ብቻ የወሰኑት ሰዎች፡ ምን ማለታቸው ነው? ምንስ ማድረጋቸው ነው? እግዚአብሔር የሠራውን፡ የጋብቻን ሥርዓት፡ ማቃለላቸው ነውን? ወይስ መናቃቸው ነውን? ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፡ ከብዙዎቹ ደቀ መዛሙርቱ መካከል፡ ለሓዋርያነት የመረጠው፡ ዮሓንስንና እርሱን የመሰሉትን ድንግላውያንን ብቻ አልነበረም። ታዲያ፡ ሚስት ካላቸው ባለትዳሮች መካከል፡ ቅዱስ ጴጥሮስን፡ ለሓዋርያነት ብቻ ሳይኾን፡ የመንግሥተ ሰማያትን ቁልፍ ያህል ላስገኘለት፡ ለሊቀ ሓዋርያነት ጭምር፡ እንዴት፡ ወይም ለምን፡ መረጠው? ጵጵስና፡ ለድንግላውያን ወይም፡ ለመነኰሳት ብቻ ቢኾን ኖሮ፡ ከቅዱስ ጴጥሮስ ይልቅ፡ በፍቅሩም ስለሚቀርበው፡ "ፍቁረ እግዚእ" የተባለውን፡ ዮሓንስን ለምን አልመረጠውም? "ጵጵስና የሚገባው፡ ለመነኰሳት ብቻ ነው" የሚሉ ወገኖች ካሉ፡ እነዚህ ወገኖች፡ ጌታን፡ "የእኛ ሥርዓት ካንተ ይበልጣል" ማለታቸው ነውን?

"የኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያና ሓዋርያ" ብሎ፡ ራሱን የሚጠራው፥ ራሱም፡ በድንግልና የኖረውና "እንደእኔ ብትኾኑ ይሻላችኋል" እስከማለት የደረሰው ጳውሎስ እንኳ፡ በመንፈስ ቅዱስ ተመልቶ፡ በጻፋቸው መልእክቶቹ፡ ስለዚህ ጉዳይ የሰጠውን መመሪያ እንስማ!

"'እሙን ነገር፡ ዘይፈቅድ ይሠየም ጳጳስ፤' ሠናየ ግብረ ፈተወ። ወባሕቱ ርቱዕ፡ ይሠየም ጳጳስ፡ ዘኢያደሉ ለገጽ፥ ዘአልቦ ምክንያት፥ ዘአሓተ ብእሲተ አውሰበ፤" ማለትም፡ "'ማንም፡ ጵጵስናን ቢፈልግ፡ መልካምን ሥራ ይመኛል' የሚለው ቃል የታመነ ነው። እንግዴህ፡ ጳጳስ፡ ሊኾን የሚገባው ሰው፡ የማይነቀፍ፥ የአንዲት ሚስት ባል፥ ልከኛ፥ ራሱን የሚገዛ፥ እንደሚገባው የሚሠራ፥ እንግዳ ተቀባይ፥ ለማስተማር የሚበቃ፥ የማይሰክር፥ የማይጨቃጨቅ፥ ነገር ግን ገር የኾነ፥ የማይከራከር፥ ገንዘብን የማይወድድ፥ በኹለንተናቸው ንጹሓን ኾነው የሚታዘዙ ልጆች ያሉት፥ ቤተሰቡን፡ በመልካም ሥርዓት የሚያስተዳድር ሊኾን ይገባዋል! ቤተሰቡን፡ በሥርዓት ማስተዳደር የማይችል ሰው፡ የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን፡ እንዴት ሊጠብቃት ይቻለዋል? በትዕቢት ተነፍቶ፡ በዲያቢሎስ ነቀፋና ወጥመድ እንዳይወድቅ፡ በውጭ ባሉት ሰዎች ዘንድ፡ መልካም ምስክርነት ያለው ሊኾን ይገባል።"

ታዲያ፥ እንዲህ ከኾነ፡ እኛ፡ ኢትዮጵያውያን፡ ከእግዚአብሔር ያገኘነውንና የራሳችን የኾነውን መለኮታዊ ሥርዓት፡ ባዕዳን አጥቂዎቻችን በኾኑት በግብፃውያን ሥርዓት ስንለውጠው፡ "እነርሱ፡ ከእነቅዱስ ጳውሎስ በላይ ያውቃሉ! እኛም እናውቃለን!" ማለታችን ነውን? ራሱ፡ ባለቤቱ ኢየሱስ ክርስቶስ፡ በዓለሙ ኅብረተሰብ መካከል ተወልዶና አድጎ በየከተማው ሳይቀር፡ እየኖረ ማስተማሩ፥ ሓዋርያቱንም፡ ከገዳማውያንና ከባሕታውያን ሳይኾን፡ ከዚያው ኅብረተሰብ መካከል መምረጡ፡ ለምን ይመስለናል? ቅዱስ ጳውሎስስ፡ ግልጽ አድርጎ፡ "ጳጳስ ኾኖ የሚሾመው ሰው፡ የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን፡ ሊጠብቃትና በሥርዓት ሊያስተዳድራት ይችል ዘንድ፡ የአንዲት ሚስት ባል የኾነ፥ በኹለንተናቸው ንጹሓን ኾነው የሚታዘዙ ልጆች ያሉት፥ ቤተሰቡን፡ በመልካም ሥርዓት የሚያስተዳድር ሊኾን ይገባዋል!" ለምን አለ?
አንድ ጳጳስ፡ በዓለሙ ውስጥ የሚኖረውን እያንዳንዱን ግለሰብ፥ ከዚያም፡ ጋብቻን፥ የባልና ሚስት ኑሮን፥ ማለትም፡ የትዳርና የቤተሰብ ሕይወትን፥ በአጠቃላይም፡ ኅብረተሰብን በሚመለከት፡ ያለውን፡ ውሳጣዊና አፍአዊ ችግር፡ በቅርብ የሚያውቅና የሚረዳ፥ ከዚህም የተነሣ፡ ለችግሩ መፍትሔን ሊያገኝ የሚችል እንዲኾን በማሰብ መኾኑን፡ ማንም ተመልካች በቀላሉ ሊገነዘበው አያዳግትም።

ዳሩ ግን፡ እግዚአብሔር፡ እንዲህ አድርጎ የሠራውን ፍጹም ሥርዓት፡ ሰዎች፡ ለራሳቸውና በእነርሱም አማካይነት፡ ለዲያቢሎስ በሚስማማ መንገድ በመለወጥ፡ ከላይ ስለተጠቀሱት፡ ስለግለሰብ፥ ስለትዳርና ስለዓለማውያን ኅብረተሰብ አኗኗርና ችግር፡ ምንም የማያውቁትን፥ ራሳቸውን፡ ከሰውና ከኅብረተሰብ ለይተው፡ የብሕትውናን ዝግ ሕይወት፥ በበረሃም የገዳማዊነትን መንፈሳዊ ኑሮ መርጠው የተቀመጡትን ሰዎች፡ ከበዓታቸው እያወጡ፡ እነርሱን ብቻ፡ ለጵጵስና ሹመት ማብቃት፡ "በእርግጥ የመንፈስ ቅዱስ ሥራ ነው" ብሎ ለመቀበል፡ ለሃይማኖታዊ ሰውነት፡ እጅግ ይከብደዋል።

እንግዴህ፡ ከቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ ተጠቅሰው፡ ከዚህ በላይ፡ በግልጽ በቀረቡት አምላካውያት ቃላት መሠረት፡ መጀመሪያ፡ በራሱ በእግዚአብሔር ተመሥርቶ፥ ኋላም፡ ራሱ፡ እግዚአብሔር ወልድ፡ በኢየሱስ ክርስቶስ ሰው ኾኖ ባጸናው፥ ተያይዞም፡ ሓዋርያትና ተከታዮቻቸው እያለመለሙት በቀጠለው የኢትዮጵያውያን ሥርዓት፡ የጵጵስና ሹመት፡ ለመነኰሳት ብቻ ሳይኾን፡ ሥልጣነ ክህነት ላላቸውና ለመንበሩ ብቁ ኾነው ለሚገኙ፡ ሕጋውያን ጭምር፡ ለኹሉም ክፍት ኾኖ ሊፈቀድ ይገባል።

+ + +
+ + +

ኢትዮጵያ፡ የዓለሙ መፋረጃ!
ከገጽ ፫፻፷፬-፫፻፷፯

Share on Google Plus

ስለ የተለጠፈበት ቀን

    Blogger Comment
    Facebook Comment