ኅማማተ 'ኢትዮጵያ'


ደራሲ ደሞዝ ጎሽሜ

ከዛሬ ትላንት ይሻላል...ይላሉ መጽሀፍ ቅዱስና ሳይንስ።...እውነት ነው.። ሀገር ከታመመች ቆይታለች። የምትወስዳቸው መድሀኒቶችም ሌላ በሽታዎች በመሆናቸው እየባሰባት እንጁ የሚሻላት አልሆነም። ትላንት ትሻል ነበር። ለምን?

፩.ዕዝራ ሱቱኤል

በመጀመሪያው መጽሀፌ ዕዝራን ተንተርሼ የዓለምን ማርጀት ከትቤ ነበር( ዓለም የምንለው ሰው ለማለት ነው)። በቅድስና(ሞራል) በስነምግባር፣ በእምነትና በትጋት ከእዝራ እነ አብርሃም እንደሚበልጡ መልአክ ይነግረዋል። በሌላ እባባል በዚህ ዓለም ስርዓት ከነገ ዛሬ ይሻላል። ከእርጅናዬ ወጣትነቴ የተሻለ ኃይልና አቅም አለው። አንድን ስልጣኔ ወስደን ብናይ በስልጣኔው መሰረታዊ ትርክት ጀማሪዎቹ ከኋለኞቹ የተሻሉ ናቸው። በከፍተኛ ሞራልና ቅድስና ተጀምሮ በመረን የለሽነት ይጠናቀቃል።

በተፈጥሮ ሀብት በኩል ሲታይም እውነታው ያው ነው። ከዛሬው ክምችት የትላንቱ ይበልጣል ። ኃይል ከጠቃሚነት ወደማንጠቀመው  የኃይል አይነትነት ይለወጣል።በመጨረሻም ፀሐይ መንደዷን ታቆማለች። ነገሩ የገነቱን ዘር አይለቅም።ገነት መጀመሪያ ጥሩ ነበር። ከዚያ አባላሸነው።ከመታዘዝ ወደ አለመታዘዝ መኮብለል 'የዘራችን' ሆኗል። 

፪. የዛሬው ክፋት

 ተወዳጁ 'የዛሬውን ክፋት ለነገ አታሳድሩ' ይላል። ነገ የራሱ በቂ ክፋት(ችግር) አለው። የዛሬን ስንደምርለት ሁለት ክፋት ይኖረዋል። የከነገወዲያው ሶስት ክፋት...አራት...አምስት...ክፋት ይከማቻል..።በልቦናችን ይነግሳል።የነፍስ መቆሸሽ ውስጥ እንገባለን። ለራሳችን ደስ አንልም።በዚህ መሰረትም ባለክምችቱ 'እኔ' ከዛሬ ትላንት እሻላለሁ። ነገ-አልባ ነኝ። ይህንን ዛሬ 'በኢትዮጵያ 'እያየነው ነን።

አውሬው ተስፋዎችን ሁሉ እያደነ በሚገድልባት ምድራችን ተስፋ መቁረጥ ነግሷል።ባከማቹት የዘመናት ክፋት የተነሳ በየቀኑ እየከፉ በሚሄዱ ሰዎች ተከበናል። በክፋት የተመረቁ ሰዎች ብርቅ አልሆን ብለውናል።

ዛሬ ያለንበት አስተዳደርና ማኅበረሰባችን ሁለቱን ኢትዮጵያዎች ያጣ ነው። የመጀመሪያውን በውጊያ፣ በካሪኩለም በልዩ ልዩ መንገድ እንዲጠፋ የተፈረደበት በተለምዶው 'ያለፈው ስርዓት' የሚባለው ነው። ሁለተኛዋ የህገ መንግስቱ የምትባለው የዛሬዋን 'ኢትዮጵያ' ናት። የለቻቸውም።

 ያፈረሱትን አልተኩትም።ከሁለት የወደቀ፣አቅጣጫው የማይታወቅ፣ቡርጭቅጭቅ ያለ ቅጥ አልባ ፖለቲካ ባለቤት ሆነናል። በእየለቱ ኑሯችን ብንተያይ፣ችግራችንን ብናወሳው በእውነት ለራሳችን እናዝናለን። በቅጡ በልተን የምናድረው ስንቶቻችን ነን? ስንቱ ትዳር ነው በሰላም ልጆቹን እያሳደገ ያለው? ባለስራዎችም ፈተና ውስጥ ነን።ስራ የሌላቸውም እንዲሁ። ሁሉ ነገር ኖሮን እንኳን ለነገው ኑሯችን እርግጠኛ አይደለንም። የዛሬው ካለፈው የባሰ ነው። ከመኖር መሞትን አቅለንዋል።ምን ይሻላል?ለምትታየው ኢትዮጵያ በጎ ሰዎች እያሉ ካሉት ውጪ ምንም አልልም።

ይሁንና በተወዳጁ ለሚያምኑትና እምነታቸውን ለሚኖሩት ግን ነገ ከዛሬ የተሻለ ነው። በእርሱ ያልዳንበት እኛነት የለንም። የንጋት ኮከብ በመሆኑ ሁልጊዜ(በጊዜም ያለ ጊዜም) ይነጋል።በእርሱ ትላንት ሽባ የነበረው ዛሬ ይራመዳል።ሞቶ የነበረው ይነሳል። የአሮጌውን ሰማይና ምድር(ስጋና ነፍስ) ስርዓት ቀይሮታል። በእርሱ ሞት ሞታችን ተወስዷል።በሞቱ እኛ ተነስተናል።

ይህችን በመቅደስ ፣በታሪክ፣በሰብእና፣በባህርይ የተመስከረች ንጹህ ሰውነት ያኔ ተቀብለናታል።በእርሷ ራሳችንን አደራጅተንባታል። ይህችን እስራኤል ዘነፍስ ኢትዮጵያ ብለናታል( የሰኔ ፲፮ቱን ክታቤን እየው)። እውቀንም ይሁን ሳናውቅ የእውነቷ ታሪካዊ ስፍራ ባለቤቶች ነን(ነበርን)።ይህ ስርዓት ያላቸው ሰማያውያን ናቸው።እንዳንመካከርና ያለንን እንዳንሰጣቸው በህገ መንግስቱ የተነሳ ምድራዊው መንግስታችንም ሆነ ያለንበት ሀገራዊ እብደት አይፈቅድልንም። ስለዚህ የሰባው ዓመት ፍጻሜ በመሆኑ የየመንፈቆቹን መከራ መካፈል ግዴታ ሆኗል(ስለምጽዓት ምስጢር በቅርቡ እናወሳ ይሆናል)። ሺህ ዓመት ስለተፈጸመ ከተማይቱን የምድር አህዛብ፣ጎግና ማጎግ(አውሮጳውያን) ከበዋል(በእውነቱ ምክንያት ድርጊቱ ለቦታውም ይተረጎማል)። መጪው ጽርኅ ጽዮን የኔ ናት የሚል ዘንዶ ከቧል። ውስጣቸው በተጠመቀ የዘመናት ክፋት ሰክረዋል።ከተማይቱን አያገኟትም። እንደቃሉም እሳት ከሰማይ ወርዶ ያጠፋቸዋል(ቃል ነው)። እንደዜጋ ምንም ተስፋ ልንሰጣቸው ያለተቻለንን ታዳጊዎች ሳስብ' ምን እያረግን ነው ?'እላለሁ።በእኛው ዘመን ዘንዶው ከሰማይ እንደተጣለ በምድር ወርዶ ውሸቱን ለቋል። የዳኑትን ባላገኘ ጊዜ ባልዳኑትና በመዳን ስራ ያሉት ዳግም እንዳይወለዱ ሀሰቱን ይለቃል። ይተፋል።አቤት የውሸት መዓት? ሁሉም ኢትዮጵያን ለማጥፋት ይጣደፋሉ።ምድር ግን ውኃውን ዋጠችው ይላል ።በትዕግስት ነው የሚዋጠው። የመንፈሱ ዋና ስራ ማናደድ ስለሆነ አለመናደድን እንያዘው። ከነገድ ከቋንቋ ተዋጀተን ሰውነትን የምናነግሰው ከጸጋ ባለመራቆት ነው።

ወይን ጠጁ አልቋል። እንኳን የሀገራችን የዓለምም ተጠናቋል። ባለቀብን ጊዜ በመካከላችን የተገኘ የእግዚአብሔር ልጅ ከኛጋ ነው።በእርሱ ሲኮን ከመጀመሪያው ወይን ጠጅ ሁለተኛው ይሻላል። በጣእሙም ይለያል። አህዛብን ሁሉ በብረት በትር የሚገዛው ወንዱ ልጅ በዚህ አለ። በእርሷ መገለጽ ምክንያት እየሆነ ያለውን እያየን ነው።እርሷን ማጥፋት አይቻልም። ምክንያቱም ስለማይቻል።አላወቅነው ይሆናል እንጂ ሁላችንም የምንፈልገው እርሷን ነው። የሰው ልጅ የባህርይ ግብ ናት። የዚህ ታላቅ እውነት 'ሸክም'ስላለብን ውጊያዎች ሁሉ ከበውናል። ወይን ጠጁ አልቋል ካልነው ቆይተናል።ባለንበት እንጽና።ከቻልን ከሕይወት ውኃ ወንዝ እንጠጣ። የኢትዮጵያን ኅማማት ያሳየን እርሱ ትንስኤዋንም አዘጋጅቶታል።ከሀሳዊ ኢትዮጵያም ይጠብቀናል።



Share on Google Plus

ስለ የተለጠፈበት ቀን

    Blogger Comment
    Facebook Comment