ስለ ትምህርት (ክፍል 3)


እለ አጽበሐ

በባለፈው ክፍል የትምህርት ስርዓቱ እንዴት አድርጎ ተማሪዎችን በክፍሎች እንደሚለያይ እና ያም ምን ጉዳት እንዳለው አይተናል። በቀጣይ ክፍሎች አንድ ጊዜ ጨምረን እንመለስበታለን፣ ለአሁን ግን አንድ ሌላ ወሳኝ ጉዳይ እናንሳ።

የትምህርት ስርዓት በተማሪዎች ማንነት እና ባህሪ ላይ የሚፈጥረውን ተጽዕኖ እንመልከት።

ይህ ስርዓት፣ ከተማሪዎች የሚጠብቀው ትክክለኛውን መልስ እንዲሰጡ ነው። አንድ ትክክለኛ መልስ ብቻ አለ፣ ከርሱ ሌላ ከመለሱ ፈተናውን አያልፉም፣ ያንን ካላላፉ ደግሞ ነጥብ ወይም ማርክ የሚባል፣ ተማሪዎችን የሚያበላልጡበት መስፈርያ አለ። ተማሪዎችም ያንን መስፈርት በደምብ እንዲያሟሉ ይጠበቃል። ለወደፊት ስራቸውም፣ ትልቅ ቦታ ለመድረስም፣ በቤተሰብ ለመወደድም ማድረግ ያለባችው ያንን ቁጥር አሟልቶ መገኘት ነው።

ያንን ለሟሟላት ደግሞ አንዱን ትክክለኛ መልስ መመለስ ይጠበቅባቸዋል። አንዳንድ ጊዜም እንደ ሂሳብ ያለ ትምህርት ከሆነ ልክ አሰራሩንም አስተማሪው ባለው መንገድ መስራት ይጠበቅባቸዋል። እናም ፈተናውን እንዴትም አድርገው የሞሉ፣ መጽሃፉ የሚለውን በትክክል ያስቀመጡ፣ ሙሉ ነጥብ ይሰጣቸዋል፣ ከክፍል ክፍል ያልፋሉ፣ ሃይስኩል ዩኒቨርሲቲ ወዘተ እያሉ ትልቅ ቦታ የመድረስ እድል ያገኛሉ። አንዳንዶች ደግሞ ፈተናውን በትክክል ሳይሰሩ ይቀሩና ይወድቃሉ ወይም ያቋርጣሉ።

እናም የትምህርት ስራቱ እንድናምን የሚፈልገው፣ ፈተናውን ሰርተው ነጥቡን ይዘው ያለፉ ሁሉ ጎበዝ ናቸው፣ በህይወታቸው የሚሳካላቸው ናቸው፣ ወዘተ የሚል ሲሆን። እነዛ የወደቁት፣ ዩኒቨርሲቲ ያልገቡት ደግሞ የአእምሮ ብቃታቸው እስከዚህም ነው፣ ወይም ዝቅተኛም ነው፣ እውቀታቸው ትንሽ ነው፣ በህይወታቸው አይሳካላቸውም የሚል አስተሳሰብ ነው።

ነገር ግን፣ ተማሪዎች በተለይም ጎበዝ የሚባሉት ያንን አምነው ተቀብለው ይሄዱና፣ ትምህርታቸው ላይ እድሜአቸውን አባክነው፣ ያ ያባከኑት ጊዜም የሆነ ፍሬ ያስገኝልኛል ብለው ተስፋ አድርገው ካለፉበት በኋላ፣ ልክ ተመርቀው ሲወጡ ደሞዝተኛ፣ ተቀጣሪ፣ በወር የተወሰነች ገንዘብ የሚጠብቁ ሆነው ይገኛሉ። በትምህርት ስርአቱ ውስጥ ነገሮችን ብዙ ስላልጠየቁ፣ ስርአቱ ያለውን መስመር ሁሉ ተከትለው ስለሄዱ፣ ታዛዥ መሆንን ጥያቄ አለመጠየቅን ስርአቱ እንዲያስቡ በሚፈልጋቸው መንገድ ብቻ ማሰብን፣ ስርአቱ ባሰመረላቸው መስመር ውስጥ ብቻ መሄድን ስለተማሩና ስለተለማመዱ፣ ወደ ስራው ዓለም ሲሄዱም ያንኑ ይደግማሉ። አለቃቸው የሚለውን በደምብ ሰምተው የሚሄዱ፣ የሚታዘዙ፣ ሚዲያው፣ መንግስት ወዘተ ሂዱ ባላቸው መስመር መሄድን፣ እውነት ነው የተባሉትን ነገር እንደ እውነት መቀበልን የራሳቸው ውስጣዊ ባህሪ እስኪሆን ድረስ ይለማመዱታል።

ያም ጥሩ ሰራተኛ፣ ታዛዥ፣ የካፒታሊስቶች ምርጥ ተከታይ፣ የሚዲያው እና የተቋማቱ ተከታይ ያደርጋቸዋል። ስለዚህ ሳይንስ ፍጹምና በቸኛው የእውቀት ምንጭ ነው፣ ሴራ ተንታኞች እውቀት የሌላቸው ደደቦች እና እብዶች ናቸው፣ ብራንዶች ተከታይ እና አድናቂ መሆን የስልጡንነት ምልክት ነው ወዘተ የሚሉ አስተሳሰቦችን ይሞላሉ፣ አእምሮአቸው በዚያ ይታጨቃል። ሌላም ሌላም እንደ ፌሚኒዝም፣ የግራ ዘመም ተራማጅ አይዲዮሎጂዎችን፣ ሊበራሊዝምን ወዘተ እንደ ፍጹም እውነት እንዲቀበሉ፣ ባህልን እና ሃይማኖትን በተቻለ መጠን ችላ እንዲሉ (ሰዎች ባህላቸውና እምነታቸውን አጥብቀው ሊይዙ ስለሚችሉ ይህኛውን የመቀበል እድላቸው እንደየሰው ይለያያል).. ሌሎችም ሌሎችም ስርአቱ እንዲቀበሉ በሚፈልጋቸው አስተሳሰቦችና አይዲዮሎጂዎች ተጠምቀው፣ እንደ ፍጹም እውነታ ተቀብለው፣ እነሱን የሚፃረር ሰውንም እንደ መጥፎ፣ ወይም ያልሰለጠነ፣ ወይም ያልበሰለ፣ ወይም የአእምሮ አስተሳሰቡ ዝቅ ያለ፣ አንዳንዴም እብድ፤ አድርገው እንዲያስቡ አእምሮአቸው (ወይም አእምሮአችን) ይቀረፃል።

በርግጥ ትምህርት ሰረአቱ ውስጥ ያላለፈው ሰውም የዚህ ተጠቂ አይደለም ማለት አይደለም፣ ነገር ግን በዚያ ውስጥ ያለፍነው ይበልጥ የዚያ ተጠቂ እንሆናለን። ምክንያቱም በአንድ በኩል ማህበረስቡ በብዛት በተማሩት ሰዎች ስለተሞላ ማንኛውም ሰው በዙሃኑ ወደ ሄዱበት ይከተላል። ሁለተኛ ደግሞ በዙ ሰዎች ትምህርትን አቋርጠው ወደ ሌላ ህይወት ቢገቡም እንኳን ለተወሰነ ዓመታትም ቢሆን መማራቸው ስለማይቀር እነሱም የ አእምሮ አጠባው ሰለባ ናቸው። ከዚህም በተጨማር ማናችንም ቢሆን ሙሉ በሙሉ ከፕሮፓጋንዳው ወይም አእምሮ አጠባው ሙሉ በሙሉ ልናመልጥ አንችልም። የምንኖረው በስርአቱ ውስጥ ነውና ጥቂትም ቢሆን የርሱ ተጽዕኖ ይኖርብናል፣ አንድም ሁለትም ነገር ስርአቱ ያለንን ነገሮች አምነን ተቀብለን ይሆናል።

የአእምሮ አጠባን ካነሳንም አይቀር፣ የትምህርት ሰርዓቱ ዋና አላማ እና ግብ ያ ነው። ይህም ደግሞ ማንኛውንም ተማሪ ሰለባ ያደርጋል። ያንን ለመረዳት አንድ የተማሪዎችን አይነት እንመልከት። የተወሰኑ ተማሪዎች፣ ራሳቸውን ችለው ማሰብ የሚችሉ፣ ትምህርት ስረአቱ ከሚሰጣቸው መረጃ ወጥተው በራሳቸው ጥያቄዎች የሚጠይቁ፣ ብዙውን ጊዜም ብሩህ አእምሮ ያላቸው ተማሪዎች አሉ። እነዚህ ተማሪዎች ገና በጊዜ፣ ዝቅተኛ ክፍል ሳሉ የትምህርት ሰርአቱ አሰራር ይገባቸዋል። በዚህ ስርአት ውስጥም የስኬት ምስጢሩ ስርአቱ የሚፈልገውን መልስ መስጠት እንደሆነ ይረዳሉ።

ስለዚህ ኢቮሉሽንን ባያምኑም እንኳ፣ ምድር የምትሽከረከር ድቡልቡል ኳስ ናት የሚለው ባያሳምናቸውም እንኳ፣ ፈተና ላይ ሲጠየቁ ግን በትክክል ፈተናው እና ፈታኙ የሚፈልጉት ያንን መልስ እንደሆነ ስለሚያውቁ ያንን ይሰጣሉ። ስለዚህ በጊዜ ሂደት ውስጥ ስርአቱ ከኔ ምንድን ነው የሚጠብቀው መልስ የሚለውን መረዳትና ያንን መልስ መስጠትን ይለማመዳሉ።

ሌሎቹ ተማሪዎች በተለይ "ጎበዝ" የሚባሉቱ፣ ብዙውን ጊዜ ስርአቱ የሚላቸውን በሙሉ እንደ ፍጹም እውነት ተቀብለው፣ ያንንም ያለ ተቃውሞ ያሰርጹታል። እነዚህም ብዙ ጊዜ የስርአቱ ፕሮፓጋንዳ ተጠቂ የመሆን እድል ያጋጥማቸዋል። ፈተናውን በደምብ መስራት ቢችሉም፣ ጽንሰ ሀሳቡን በደምብ ቢያውቁትም፣ ነገር ግን በትምህርቱ ውስጥ የሚቀላቀለውን ውሸት ግን ለይተው ለማውጣት ይቸገራሉ። ከሌላው ተማሪ የላቀ የአእምሮ ብቃት ኖሯቸው ግን ደግሞ የስርአቱ የአእምሮ መቆጣጠርያ ቴክኒኮች ሰለባ ይሆናሉ። ስርአቱ ሲዋሻቸው "ለምን? እንዴት?" ብለው መጠየቅን ወይ ገና ድሮ ትተውታል፣ ወይም እነዛን ጥያቄዎች ወደጎን መተውን ተለማምደዋል። ምናልባትም ያንን መጠየቅ ቤተሰብና መምህራን ማህበረሰቡም ከነሱ የሚጠብቀውን ነገር እያሰቡ፣ እነዛን ጥያቄዎች መጠየቅ ደግሞ ነጥባቸውን እንደሚቀንስባቸው፣ በሰውም ሁሉ ዘንድ ጥሩ ስም ስለማያሰጣቸው (እንደዛ የሚጠይቁት ብዙም ብሩህ አእምሮ የሌላቸው ወይም ጎበዝ ያልሆኑት ተብሎ ስለሚታሰብ) በነዚህ ምክንያቶች የስርአቱን የአእምሮ አጠባ ፈተና ላይ ሞልቶ መሸለም ብቻ ሳይሆን እንደ እውነትም ይቀበሉታል።

በዚህ ሁኔታ ሌሎቹም ተማሪዎች እንደ ጎበዞቹ ተማሪዎች መሆን ከፈለጉ ስርአቱ ባሰመረው መንገድ መሄድ እና እርሱ እውነት ነው ያለውን እውነት ማለትን ይለማመዳሉ። ጥሩ ነጥብ ለማግኘት ብለው ቢጥሩም ጥረታቸው ስርአቱ ትክክል ነው ያላቸውን መልስ መመለስ፣ እውነት ነው ያለውን እውነት ማለት ስለሆነ፣ እርሱ የሚፈልጋቸውን መልሶች መሸምደድና እነዛንም ፈተና ላይ ማስቀመጥን ይለማመዳሉ፣ ያንንም ለማድረግ ይገደዳሉ። በዚህም ሁኔታ ከስርአቱ ጋ ተመሳስሎ መኖርን፣ ለመመሳሰልም የራስን መልክና ቅርጽ መቀየርን (conformism)ን ባህሪያቸው ያደርጋሉ።
Share on Google Plus

ስለ የተለጠፈበት ቀን

    Blogger Comment
    Facebook Comment