የጤፍ ባለቤትነት መብት ከኢትዮጵያ እጅ እንዴት ወጣ?

እንጀራ




Image copyrightEDDIE GERALD

ከ2000 ዓመታት በላይ ኢትዮጵያውያን ጤፍን በዋነኛ የምግብ ምንጭነት ሲጠቀሙበት ኖረዋል። ታዲያ እንዴት አንድ የደች ዜጋ በቀላሉ የጤፍ የባለቤትነት መብትን ሊያገኝ ቻለ?
በጎርጎሳውያኑ 1980ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ በኢትዮጵያ ተከስቶ የነበረውን ድርቅ ተከትሎ በምግብ እጥረት የተጎዱ ህጻናት ምስል በመላው ዓለም በሚገኙ ምግብ ቤቶች ጭምር እየተለጠፈ በረድኤት ድርጅቶች አማካይነት ገንዘብ ተሰብስቧል።
በርካቶችም ምስሎቹን ተመልክተው የገንዘብ ድጋፍ ማድረጋቸው ጠቃሚ ቢሆንም በተለይ ምዕራባውያኑ የትኛውም ጎጂ ንጥረ ነገር የሌለው የምግብ አማራጭ ከዛች አገር ይገኛል ብለው እንዳያስቡ አድርጓቸዋል።
ጤፍን የተቀረው ዓለም የምግቦች ሁሉ ታላቅ ወይም 'ሱፐር ፉድ' እያለ ነው የሚጠሩት።
ምድራችን በምታበቅላቸው አብዛኛዎቹ ሰብሎች ውስጥ የሚገኘውና በተለይ አውሮፓውያኑ ለጤና አስጊ ነው ብለው የሚፈሩት 'ግሉተን' ንጥረ ነገር በጤፍ ውስጥ አለመገኘቱ ደግሞ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ተፈላጊነቱ ከፍ እንዲል አድርጎታል።
በኢትዮጵያና በኤርትራ ለ2000 ሺ ዓመታት ሲበቅል የነበረው ጤፍ ከፍተኛ ፕሮቲን፣ አይረን፣ ፋይበርና ሌሎች ጠቃሚ ንጥረነገሮች በውስጡ ስለመያዙ ተመስክሮለታል።
የቢቢሲዋ አንጄላ ሳውሪን ወደ ኢትዮጵያ በተጓዘችበት ወቅት ወዲያውኑ በእንጀራ ፍቅር እንደወደቀች ትገልጻለች።
'' ኮምጠጥ ያለው ጣእሙና የትኛውም ዓለም ላይ የሌለው አይነት አሰራሩ ብዙ ጥያቄዎችን እንድጠይቅ አድርጎኛል። እንዴት ነው የሚሰሩት? ለምን የተለየ ጣእም ኖረው? ለምንስ ሰፋ ባለ ትሪ ሰብሰብ ብለው ይበሉታል? በጣም አስገራሚ ነው።''
'' እንጀራውን ከተለያዩ አትክልትና ስጋ ጋር አቀላቅለው ሲመገቡት ደግሞ በጣም ይጣፍጣል። እኔም ስሞክረው ደስ ብሎኛል። እንጀራውን ቆርሼ ከወጡ ጋር አቀላቅሎ መመገብ ለአያያዝ ትንሽ አስቸግሮኝ ነበር'' ብላለች።
ይህን ያክል ተወዳጅነትና ከእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ህይወት ጋር ከፍተኛ ቁርኝት ኖሮት እንዴት ጤፍን የማቀነባበርና ምርቶቹን የመሸጥ መብት በኔዘርላንድ ለሚገኝ ድርጅት ተሰጠ? ብላ ትጠይቃለች አንጄላ።

ለሁለት ሳምንታት በዘለቀው ቆይታዋ "ኢትዮጵያውያን በቀን አንድ ጊዜ እንኳን እንጀራን ሳይመገቡ አላየሁም" የምትለው አንጄላ "ጤፍን በተለያየ መልኩ የመመገብ ፍላጎት ያላቸው እንኳን አይመስለኝም" ስትል ለእንጀራ የሚሰጠውን ክብር ገልጻለች።
በጎርጎሳውያኑ 2003 የኢትዮጵያ ብዝኃ-ህይወት ኢንስቲትዩት ከኔዘርላንዳዊው የአፈርና እጽዋት ባለሙያ ጃንስ ሩስጄን ይሰራ ነበር። በዚሁም አጋጣሚ ነበር ኢንስቲትዩቱ ለምርምርና ስርጸት ይረዳል ብሎ በርካታ የጤፍ ዝርያዎችን ለዚሁ ባለሙያ ወደ ኔዘርላንድስ የላከው። ይህ ግለሰብ የጤፍን ምርቶች ለማሳደግ በሚልም ነበር ስምምነት የፈጠረው።
ከአራት ዓመታት በኋላ ግን በአውሮፓ የባለቤትነት መብት የሚሰጠው ድርጅት 'ሄልዝ ኤንድ ፐርፎርማንስ ፉድ ኢንተርናሽናል' ወይም በአጭሩ 'ኤችፒኤፍአይ' ለተባለው ድርጅት የጤፍን ባለቤትነት መብት ሰጠው።
በዚህም ድርጅቱ ጤፍን የማምረት፣ የማቀነባበርና ከጤፍ የተሰሩ የተለያዩ ምርቶችን የመሸጥ መብት አግኝቷል።
ከወራት በፊትም በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ፍፁም አረጋ በትዊተር ገፃቸው ላይ የሄግ ዓለም አቀፍ የገላጋይ ድርጅት የጤፍ ባለቤትነት ይዞት የነበረው ድርጅት መብቱ መቀማቱን ጠቅሰው ለኢትዮጵያ ከፍተኛ ድል እንደሆነ የደስታ መልዕክት አስተላልፈው ነበር።
በዚሁ ትዊተር ገፅ ላይ የደች ፍርድ ቤት ውሳኔንም አብረው አያይዘውታል።
በኋላ ላይ ግን ይህ ጉዳይ ከኢትዮጵያ ጋር በጭራሽ እንደማይገናኝና በሁለት የደች ኩባንያዎች መካከል የተካሄደ የጥቅም ክርክር እንደሆነ ተገልጿል።
በሆላንድ የጤፍ ዱቄት አዘገጃጀት ላይ በባለቤትነት የተመዘገበው ኤንሺየንት ግሬይንስ የተባለ ኩባንያ ፍቃዴን ሳይጠይቅ የባለቤትነት መብቴን ተጋፍቷል ያለውን ቤክልስ የተባለ በጤፍ ምርቶች ዳቦና ኩኪስ የሚያመርት ድርጅት ላይ ክስ መስርቷል።
በዚህም የሎያሊቲ (የባለቤትነት መብት) ክፍያ ሊከፈለኝ ይገባል፤ ለፈጠራዬ ገንዘብ ይሰጠኝ የሚል ክስ ማቅረቡን ተከትሎ፤ በምላሹ ቤክልስ የተሰኘው ድርጅት የባለቤትነት መብቱ ሊሰጠው አይገባም፤ ምክንያቱም አዲስ ፈጠራን ስላልጨመረ የባለቤትነት መብቱ ሊነጠቅ ይገባል የሚል መከራከሪያን ይዞ ቀርቧል።
ፍርድ ቤቱም ኤንሺየንት ግሬይንስ የተባለው ድርጅት ምንም አይነት አዲስ ነገር ባለመጨመሩ የባለቤትነት መብቱን ከመንጠቅ በተጨማሪ ቤክልስ የተሰኘው ድርጅት ላወጣው ወጪ በሙሉ ካሳ እንዲከፈል ውሳኔ አስተላልፏል።

ኢትዮጵያ ከባለቤትነት መብት ጋር በተገናኘ ዓለም አቀፍ ክርክር ውስጥ ስትገባ ይህ የመጀመሪያዋ አይደለም። ከታዋቂው የአሜሪካ ቡና ሻጭ 'ስታርባክስ' ጋር በይርጋ ጨፌ ባለቤትነት ጋር በተያያዘ ዓለማቀፍ ገላጋይ ፍርድ ቤት ሄዳ ነበር።
ከበርካታ ድርድሮች በኋላም በጎርጎሳውያኑ 2007 ስታርባክስ የሀረር፣ሲዳማ እና ይርጋጨፌ ቡናዎችን እንዲያስተዋውቅና እንዲሸጥ ስምምነት ላይ መደረስ ተችሏል። በዚህ ክርክር መሀል ግን የኢትዮጵያ የቡና ዋጋ በዓለማቀፍ ገበያው ከፍ እንዲል ረድቶታል።
የአገር በቀል ሰብሎች ባለሙያ የሆኑት ዶክተር ቡላ ወዬሳ እንደሚሉት የኔዘርላንዱ ድርጅት በሚሊየን የሚቆጠሩ የኢትዮጵያ ገበሬዎችን የባለቤትነት መብት የነጠቀ ነው ብለዋል።

ምንጭ፦ BBC News አማርኛ

Share on Google Plus

ስለ የተለጠፈበት ቀን

    Blogger Comment
    Facebook Comment