የኢትዮጵያ ጠላት ግራኝ ዐቢይ አሕመድ በሥራ ሰበብ ኢትዮጵያውያንን ከቅድስት ሀገራቸው ሊያስወጣ ነው

የኮንስትራክሽን ሠራተኞችወደ መካከለኛው ምሥራቅ የሥራ ስምሪት መጀመሩንና ወደ እስያና አውሮፓም የሠለጠነ የሰው ኃይል ለመላክ ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ እንደሆነ በሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የውጭ አገር ሥራ ስምሪት ዳይሬክተር ጀኔራል ብርሃኑ አበራ ለቢቢሲ ገለፁ።

በዚህ የውጭ ሃገር ሥራ ስምሪት በተለይ በኮንስትራክሽን ሙያ ላይ እውቀቱና ልምዱ ያላቸውን ባለሙያዎችን ለመላክ እንደታሰበም አቶ ብርሃኑ ተናግረዋል። ይሁን እንጂ ሥራ ቀጣሪው የሚፈልገው የሥራ ዘርፍ ስላልተገለጸ በየትኞቹ የኮንስትራክሽን ዘርፎች ላይ እንደሆነ ዝርዝሩን ገና አለመለየታቸውን አክለዋል።

ይህንንም ለማድረግ የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የሥራ ፈጠራ ኮሚሽንና የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የተካተቱበት የጋራ ኮሚቴ መቋቋሙን ገልጸዋል።
ኮሚቴው የተለያዩ ሃገራትን የሠራተኛ ፍላጎት ያጠና ሲሆን ፖላንድ፣ ጃፓን፣ ካናዳ፣ ጀርመንና ሩሲያ ከፍተኛ የሰው ኃይል ፍላጎት እንዳላቸው ተለይቷል።
በመሆኑም ወደ እነዚህ ሃገራት በፍጥነት ሠራተኛ ይላካል ተብሎ ታሳቢ መደረጉን አቶ ብርሃኑ ይናገራሉ። ዳይሬክተሩ እንደሚሉት ጃፓን ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም ሃገራት ክፍት የሆነ 350 ሺህ የሥራ እድል እንዳላት አስታውቃለች። ይህንን እድል ለመጠቀምም የስምምነት ሰነድ ተዘጋጅቶ መላኩንም ገልጸዋል።
በተመሳሳይ መልኩ ካናዳም ከ150 ሺህ ያላነሰ የሥራ እድል እንዳለ የተገለፀ ሲሆን ይህንን ታሳቢ አድርጎ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑንም አክለዋል።
ይህ የሥራ እድል በመላ ኢትዮጵያ ለሚገኙ ተወዳዳሪዎች በእኩል መልኩ የሚቀርብ ሲሆን የመምረጫ መስፈርቱም የተፈለገው የሥራ ዓይነት ከተለየ በኋላ የሚወሰን እንደሚሆን ገልፀውልናል።
የሥራ ስምሪቱ በአንድ ጊዜ ብቻ ተልኮ የሚቋረጥ ሳይሆን ወደተለያዩ ሃገራት እየሰፋ እንደሚሄድም ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል።
በቅርቡ 13 ሠራተኞች ወደ ኳታር፣ 6 ሠራተኞች ደግሞ ወደ ዮርዳኖስ የተላኩ ሲሆን ወደ ሳዑዲ አረቢያ 58 ሠራተኞችን ለመላክ ዝግጅት መጠናቀቁን ገልፀዋል።
እነዚህ ግለሰቦች በቤት ሠራተኝነት የሚሰማሩ ሲሆን ሕጋዊ ፈቃድ በተሰጣቸው ኤጀንሲዎች የተለዩ ናቸው።
በተለይ በአረብ ሃገራት በአሠሪና ሠራተኛ መካከል በሚፈጠሩ ችግሮች በርካቶች ለእስርና ለእንግልት የተዳረጉ ሲሆን በቅርቡም በርካቶች ወደ ሃገራቸው መመለሳቸውና በዚህም ምክንያት የውጭ ሃገር የሥራ ስምሪት ታግዶ መቆየቱ አይዘነጋም።
አሁንም እንደዚህ ዓይነት ችግሮች እንዳይከሰቱ ምን ሰርታችኋል? ያልናቸው ዳይሬክተሩ ከተቀባይ ሃገራት መንግሥታት ጋር የሁለትዮሽ ስምምነት ለማድረግ የተወሰነው እንደዚህ ዓይነት ችግሮችን ለመፍታት ነው ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
ከዚህ በፊት ታግዶ የነበረው የውጭ ሃገር ሥራ ስምሪት የሕግ ማዕቀፍ ውስጥ ያሉ ችግሮችንና የአደረጃጀት ክፍተቶችም ቀድመው ተፈተዋል ብለዋል።
በመሆኑም በሁለትዮሽ ስምምነቱ ተቀባይም ሆነ ላኪ ሃገራት የሚወስዱት ኃላፊነት በመኖሩ እንደዚህ ዓይነት ችግሮች እንደማያጋጥሙ አረጋግጠዋል።
ከዚህም በተጨማሪ በሕጋዊ መንገድ ከሄዱ በኋላ ባሉበት የሚያጋጥማቸውን ማንኛውንም ጉዳይ ሆነ ችግር ሊከታታልና ችግራቸውን ሊፈታ የሚችል ባለሙያ [Labour attache] በየሃገራቱ ለመመደብ ዝግጅት መጠናቀቁን ገልፀዋል።
ባለሙያዎቹ የሥራ ገበያውን ከማጥናት ባሻገር የዜጎችን መብትና ደህንነት እየተከታተሉ ደህንነታቸው ተጠብቆ እንዲሰሩ ክትትል ያደርጋሉ። "ባለሙያዎቹ ከጥቂት ወራት በኋላ ይመደባሉ" ብለዋል።
ስለ ሥራው ዘላቂነት በተመለከተ ሃሳብ ያነሳንላቸው አቶ ብርሃኑ የሚደረገው የሥራ ውል ኮንትራት [ጊዜያዊ] ቢሆንም እንደሁኔታው የሚታደስባቸው አጋጣሚዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ አስረድተዋል።
በኢትዯጵያ የሥራ አጦች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ እንደሆነ በተለያየ ጊዜ የሚወጡ መረጃዎች ያመላክታሉ።
ይሁን እንጂ በዚህ መልኩ በተለያየ ደረጃ የተማሩ ሰዎችን ወደ ውጭ ሃገራት መላክ የሃገር ውስጥ አቅምን አያዳክምም ወይ ያልናቸው ዳይሬክተሩ፤ "የመንግሥት አቅጣጫ ዜጎች በሃገራቸው ላይ ሰርተው መለወጥ እንዲችሉ ቢሆንም ወደ ውጭ ሃገር ሄደው ሠርተው መለወጥ ለሚፈልጉ መብታቸው፣ ክብራቸውና ደህንነታቸው ተጠብቆ መሄድ እንዲችሉ ነው እየተሰራ ያለው" ብለዋል።
ከዚህም ባሻገር በሃገር ውስጥ ያለውን የሠራተኛ ፍላጎት አርክቶ ለሚተርፈው ደግሞ የሥራ እድሉን መፍጠር እንደሚያስፈልግ አስተያታቸውን ሰጥተዋል።
በቅርቡ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ 50 ሺህ የሚጠጉ ሠራተኞችን ወደ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ለመላክ እቅድ እንደተያዘ አስታውቀው ነበር። ይህም ብቻ ሳይሆን ወደ ኤዥያና አውሮፓ ሃገራትም የሠለጠነ የሰው ኃይል ለመላክ እንደታሰበ መናገራቸው ይታወሳል።

የዜናው ምንጭ፦ BBC አማርኛ
Share on Google Plus

ስለ የተለጠፈበት ቀን

    Blogger Comment
    Facebook Comment