ቤተክርስቲያን የእናንተ ናት እንጂ የቄሶች አይደለችም‼️


ቤተክርስቲያን የእናንተ  ናት  እንጂ  የቄሶች  አይደለችም ‼️ የካህናትም አይደለችም  የምዕመናን  ናት  ምዕመናን  በገንዘባቸው  ያቆሟት ናት  ካህናት  ተቀጣሪዎች  ናቸው  ሠራተኞች  ናቸው‼️

እግዚአብሔር  እንደሚፈርደውም አልጠራጠርም  ፍርዱን እጠብቃለሁ  ነገር  ግን እናንተ  በዛው ባላችሁበት  አጥቢያ  ተወያይታችሁ  ሃሳባችሁን  መወሰን  ትችላላችሁ  ቤተክርስቲያን  የእናንተ  ናት  እንጂ  የቄሶች  አይደለችም  የካህናትም አይደለችም  የምዕመናን  ናት  ምዕመናን  በገንዘባቸው  ያቆሟት ናት  ካህናት  ተቀጣሪዎች  ናቸው  ሠራተኞች  ናቸው  ዐመላቸው ቢያምር አኑሯቸው እምቢ  ካሉ አባሯቸው ። ምንድን ነው  ? ሃይማኖት  አልባ ቄስ  ምን  ሊኾን ነው  አያርስ አይቆፍር ምን  ሊያደርግ ነው  ታዲያ ? ለዚህ  ካላገለገላችሁ ለዚህ  ካልኾናችሁ ምን  ሊኾናችሁ ታዲያ ብትጠይቁ ከእኔ የምታገኙት የለም  ይኸው  ነው  ለሃይማኖታችሁ በየራሳችሁ  ቁሙ አይ ምንም  ማድረግ  አንችልም  ካላችሁ አትበሳጩ ልማድ ቀረብን ብላችሁ አትጨነቁ  አትዘኑ ቤታችሁም የእግዚአብሔር  ቤት  ነው  ሥጋውን  ደሙን  ተቀብላችኋል የክርስቶስ  አካል ኾናችኋል ሥጋዬን የበላ ደሜን  የጠጣ እኔ  ከርሱ  ጋር እኖራለሁ  እሱም  ከእኔ ጋር ይኖራል  ብሏል ሥጋውን  ደሙን  መቀበላችን የእሱ አካል ለመኾን ነው ክርስቲያን ኹሉ የእርሱ አካል  ኾኗል የምንቸገርበት ነገር  የለም አኹን እነርሱ እምቢ ብለው ቢያምጹ እግዚአብሔር  ቀን አምጥቶ   ቤቱን የተዘጋውን ቤት ይከፍተዋል ስለ  ቤቱ ዝም አይልም ይናገራል ሲኾን ዛሬ ያለዚያ ነገ ይናገራል  እስከዚያው ድረስ በተመቻችሁ ጊዜ ቤተክርስቲያናችሁን እጅ እየነሳችሁ በተቀረ እግራችሁን  ሰብስባችሁ ቁጭ በሉ ገንዘባችሁን አትርጩ ጠላ አትጥመቁ ዳቦ አትጋግሩ ከሰማችሁኝ ይኸው  ነው መድኃኒቱ፡፡

 ግን  ለመሰላችሁ ንገሩ እናንተም ተመሩበት አለዚያ እንደው እኛ ለምን  ብለን እንደኾነ  እንኾናለን ካላችሁ የራሳችሁን ውሳኔ ነው እንጂ ከኔ የምትጠይቁት ነገር የለም ለሁላችንም ትልቅ ፈተና ነው የኾነው ጳጳሳት ካህናት ሕዝባቸውን ትተው ሲያምጹ ሕዝቡም መድረሻ ሲያጣ ባህታውያንም መንገድ አለይ ብለው ሲያስቸግሩ ይህ መቼም ትልቅ ፈተና ነው ያለንበት ስለዚህ እግዚአብሔር ረድቶን መንገድ እስከሰጠን ድረስ እኔም  ፫ ዓመቴ ነው ከዚህች ከቤቴ ውጭ የትም ቦታ ደርሼ አላውቅም እዚህ  ኾኜ ነው አቤት አቤት የምል እንደ  ዕንቁራሪት እናንተም እኔን መስላችሁ መኖር የምትችሉ ከኾነ ሞክሩ የማትችሉ ከኾነ የመሰላችሁን ማድረግ የእናንተ ፋንታ ነው እኔ ግን ሃሳቤ እዚህ ድረስ የተናገርኩት ነው ዝርዝር ጉዳዩ ይሄ ነው በኢትዮጵያ ጉዳይ ግን ያለ ሃይማኖት ምንም ሊኾን አይችልም !!! 

ካህናት ድሮ አትርሱኝ ይባሉ ነበር አንድ ነገር ሲመጣ ዛሬ ግን ብር ነው  የሚሰጡ ብር ይሰጡ ጀመር እንደኔ እንደኔ ቢኾን እኔ የመንግሥት አባል ብኾን ኖሮ የካህናትን ብር አልቀበልም ነበር የዐመፅ ብር ነው ጉዳት ያስከትላል እንጂ የሚሰጠው ጥቅም የለም እነሱ ጸልየው ያልጠቀሙ በገንዘብ ሊጠቅሙ የእግዚአብሔርን ገንዘብ ሰርቀው ሊጠቅሙ ነው ገንዘቡ የእግዚአብሔር ነው አትስረቁ ብሎ የሚያስተምር ቄስ ይሰርቃል ?  ሰርቆ ለሌላ ይሰጣል እና ይሄ በፍጹም አፈጻጸሙ ኹሉ አሰራራቸው ኹሉ በተለይ  የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አባሎች የኾንን ኹሉ ከካህናቱ እስከ ሕዝቡ ድረስ ከሕዝቡ እስከ ካህናቱ ድረስ የምንሰራውን ማወቅ አልቻልንም አልቻልንም እንዴ ስንታገል አብራችሁ ካልቆማችሁ ምኑን ነው መቆም የምንችለው በሐምሌ  ዘመቻ ፊልጶስ ብሎ ፕሮቴስታንት ዐወጀ ተቃወምን ( ይህን  የተናገሩት በ፲፱፻፺ ዓ.ም ነው ) እስካሁን ይህን  ይዘው ነው መከራ የሚያበሉን እግዚአብሔር ግን ነገሩን አስቀረው እነሱ ግን አሁንም ቢኾን እንደዛ እያደረጉ ነው እመቤታችንን እየተሳደቡ ነው ሚስቱን የሚፈራ ፕሮቴስታንት ሚስቱን የሚያከብር ፕሮቴስታንት ለሚስቱ የሚታጠቅ የሚፈታ ፕሮቴስታንት እመቤታችንን ይሳደባል ጨካኝ !!! ይህ ኹሉ መዓቱ የት ላይ ነው ? ኹላችንም ላይ ለምን መጣ ? እንዴት መጣ ? የሚፈታውስ በጸሎት ነው ? በገንዘብ ነው ? በጒልበት ነው ? በፓለቲካ ነው ? በየትኛው ነው ? የሚፈታው ጦርነቱ ነው ዕርቁ ነው የሚያዋጣው (በኢትዮጵያና በኤርትራ በጊዜው ተነስቶ የነበረው ጦርነትን የሚመለከት ነው ) የትኛው ነው  የሚያዋጣው ኹሉም  መላ የለውም ዕርቁም ዕርቅ ሊኾን አይችልም (አኹን  ከኤርትራ  ጋራ ያለንን ውሉ ያለየውን  ግንኙነት ልብ ይሏል) 
    
         በአንድ አካባቢ  ዋርካ ዛፍ ሥር ተወሽቆ የሚኖር ዘንዶ ነበር አሉ በአካባቢው እንስሳት ትንሹም ትልቁም ይሰማራሉ እሱ ግን ማንንም አይነካም ሲያስፈልገው ብቻ ፀሐይ ሞቆ ተመልሶ ይገባል አፈር እየላሰ ነው የሚኖር ከእለታት አንድ ቀን አንዱ ተንኮለኛ እረኛ ተንኮል አስቦ የትአባቱንስና ይህንን ዘንዶ አንገቱን ነው የምቆርጠው ብሎ መጥረቢያ ስሎ ይመጣና ሊያጎብርበት ሲዘጋጅ ለካ ዘንዶው ቀድሞ ዐይቶ ኑሮ ቶሎ ወደ ጎሬው ይገባል  ይገባና አይይይ እንደው ምን አልኳቸውና ነው አሁን  ለክፉ የሚያስቡኝ ከብቶቻቸውን አልነካው ልጆቻቸውን አልነካሁ ለምንድን ነው ብሎ ሲያስብ ከእንግዲህ ዝምድና ከሌለን ብሎ እንስሶችን አንድ አንድ ይነጥቅ ጀመር እነሱም ማዳን አልቻሉም እየባሰ ሄደ ነገሩና በመካከላቸው አንድ አስታራቂ ይነሳና ታረቁ እንደቀድሞአችሁ ኑሩ ብሎ ይጠይቃል እነሱ እሺ ይላሉ ዘንዶው ሲጠየቅ አይ መታረቁን እታረቅ ነበር ግን ዕርቁ ዕርቅ አይሆንም ይላቸዋል ምነው ሲሉትም እኔም ያቺ የቃጡብኝ መጥረቢያ ሁልጊዜ ከልቤ አትጠፋም እነሱም ደግሞ የፈጀሁባቸው ከብቶቻቸውን ከልባቸው ስለማይጠፋ ዕርቁ ዕርቅ አይሆንም አለ ይባላል ።

      ያ የፈሰሰ ደም እንዴት ተብሎ ታጥቦ ነው ዕርቅ ወደፊት የሚመሰረተው ይኾናል ? አይኾንም !!! ይሄ እኮ ሊሆን የሚችለው ሃይማኖት ሲኖር ነው ይሄ እኮ ሊሆን የሚችለው ቤተክርስቲያን ስትኖር እኮ ነው ይሄ እኮ ሊሆን የሚችለው ካህናት መነኰሳት ጳጳሳት መሃል ገብተው አንተስ ምንድን ነህ አንተስ ምንድን ነህ ለምንድነው ሰይፍ የምትመዝዝ መጀመሪያ እኛን ገለህ ነው እዚያ ሰይፍ የምትሰነዝር ብለው ቢቆሙ ኖሮ ያም ሃይማኖት  ቢኖረው ኖሮ ነበር ።

ቤተክርስቲያኒቱ ሃይማኖት የላትም ቤተመንግሥቱም ሃይማኖት የለው ግራና ቀኝ ኹለቱም ቅጥ የሌለው ነው ይሄው ጥፋት የመጣው አሁንም ከእግዚአብሔር ስለተለየን እንጂ ወደ እግዚአብሔር ከተመለስን እሱ መፍትሔ ሊሰጠው ይችላል አዎ ከተመለስን እሱም መፍትሔ ሊሰጠው ይችላል እና እየባሰ እየጨመረ መልክ እየለወጠ እንዳይሄድ ነው መስጋት ያለብን መጸለይ ጠንካራ ጸሎት ያስፈልገናል እንባችንን ማፍሰስ ያስፈልገናል የኢትዮጵያ ሕዝብ አልቆ ሀገሪቱን ብቻ የሚፈልጉ ሰዎች አሉ !!! መንግሥታትም አሉ !!! 

ሞሶሎኒ ለጣሊያን ሕዝብ ባደረገው ንግግር የፋሽስት ጦሩን ሲያዘጋጅ ፀሐይ የምትሞቁበት ሀገር አዘጋጅላችኋለሁ ነው ያላቸው ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ናት መድፉን መትረየሱን አውሮፕላኑን ባርካ የላከችው ዛሬ ባለቤት ነኝ የምትለው የኤርትራም ጦርነት በዚሁ ምክንያት እንጂ ሌላ ምንም ምክንያት የለውም ( ኢትዮጵያ ወይም ሞት ብለው ነው መጀመሪያ የገቡት ) ኤርትራ የሚባል መንግሥት የለም ኢትዮጵያና ኤርትራ የሚባል ድንበር የለም አንድ ቤተሰብ አንድ እናት አንድ ልጅ ነው  ይሄ ኹሉ የኾነው በሃይማኖት  ነው  የሃይማኖታውያን መርዝ ነው ።

ወልደ አብ ወልደ ማርያም የተባለ  ፕሮቴስታንት ነው መጀመሪያ ጥይት ተኩሶ መገንጠል ያስፈልገናል ብሎ የወጣው ከዚያ የተነሳ ጥንስስ ነው  እዚህ የደረሰው ።

እንግዲህ ብዙ ብዙ መናገር ይቻላል ግን ምን ይኾናል ትርፉ ሽሙጥ ብቻ ነው እንጂ የሚጠቅም ነገር አይኖረውም እንጂ የሚሰማ ካለ ዛሬም ቢሆን መጀመሪያ መመለስ ያለበት ሃይማኖቱ ነው መጀመሪያ መቆም ያለባት ቤተክርስቲያኒቱ ናት ለቤተክርስቲያኒቱ የሚቆሙ ሰዎች ያስፈልጋሉ ቤተመቅደሱ ተረግጧል ሥጋወደሙ መሳቂያ መሳለቂያ ኾኗል በቪዲዮ ነው የሚቀደሰው ድምጻቸውን በካሴት መስረቅረቁን ማማር መቅጠን መወፈሩን እያጠኑ እያዳመጡ መልካቸውን በቪዲዮ እየተመለከቱ ነው የሚቀድሱ ይህን ታውቃላችሁ ከእኔ የበለጠ እናንተ የዐይን ምስክሮች ናችሁ(የጸሎት  መርሃ ግብር ብለው ከመናፍቃን ጋር አብረው ውሉ ያለየ ጩኸት በቴሌዢን ሲያሾፉ የከረሙትን የሃይማት አባት ተብዬዎችን ይመለከታል) እግዚአብሔርን ልታስተባብሉት አትችሉም በግልጽ ያለ መጋረጃ ነው የሚቀደሰው ድሮ እንዲህ አይደለም እያንዳንዳችን በአሁኑ ጊዜ ድሃም ይሁን ባዕለጠጋ የገበታ ቤት ክብር አለው የዚያን ያህል እንኳን ቤተመቅደሱ ተነፍጎት ይሄ ጨዋታ ነው የሚቀደሰው ያሏችሁ ቀሳውስት ዲያቆናት ምን ያህል ነው ጥንቃቄያቸው ለቤተክርስቲያን ይሄ ካልተመለሰ በስተቀር ኢትዮጵያ ምሕረት አታገኝም ። 

ይልቁንም ኹሉም ውጭ ነው ያለው ጅራፍ ያለው ስለሆነ ኹሉም  በየበኩሉ  እየተሻማ ያለው ኢትዮጵያን አጥፍቶ የራሱ ለማድረግ ነው የሚጥረው አሜሪካ የኢትዮጵያ ወዳጅ አይደለም እስራኤል የኢትዮጵያ ወዳጅ አይደለም እስላምም የኢትዮጵያ ወዳጅ አይደለም ካቶሊክ ፕሮቴስታንት የኢትዮጵያ ወዳጆች አይደሉም ኢትዮጵያን ለማጥፋት የተዘጋጁ ናቸው ነፃነት ተሰጠኝ ክብር አገኘሁ ብሎ እኮ የሚያምን አላገኘንም ኹሉም በየበኩሉ እንደገና ለማፍረስ ሲጥሩ ሲጣጣሩ ከሚታዩ በስተቀር ይበቃናል ብለው ያመሰገኑበት ጊዜ  የለም ለምሳሌ እስላሞች  እያደጉ ነው የሄዱ አሁን እስላም ባለስልጣኖች ምን ያህል ብዛት እንዳላቸው ታውቃላችሁ ስፋቱ እንዴት እንደሆነ የበዓሉ አከባበር መልክ እንደለወጠ ታውቃላችሁ የዛሬ ዓመት ከኅዳር  ፳፮_፴  ፲፱፻፹፱  ዓ.ም ትግራይ በተደረገው ሲምፓዚየም ምንድን ነው ያሉ አዲሲቱን መካ በኢትዮጵያ እንመሰርታለን ነው  ያሉ የእኛ ናት አይደለም ያሉ የኛ ናት ሀገራችንን እንጠብቃለን አይደለም ያሉ አዲሲቱ መካን ማለት ምን ማለት ነው ? ኢትዮጵያ የሳዑዲ ዓረቢያ ቅኝ ግዛት መሆን አለባት ማለት ነው ሌላ ትርጉም የለውም ይኸው ነው የኹሉም ሃሳብ እና  እንዴት ነው ኹሉም  የሚያስበን ???

ግዛኝ ብለው ለመሸጥ አሰበኝ እንደሚባለው  ነው  ዕድላችን ኾኖ የሃይማኖት መብት ያገኘ ኹሉ ለራሱ ሀገር ኢትዮጵያን ቅኝ ግዛት ለማድረግ እንጂ ኢትዮጵያዊን በኢትዮጵያዊነቱ አምኖ ከኢትዮጽያውያን  ወንድሞቹ ጋራ በሀገሩ ደስ ብሎት ለመኖር ፍላጎት ያለው የለም ይህንን ነው ማወቅ ያለባችሁ ።

ኧረ ተው ዳማ ችላው ምንድን ነው 
ኧረ ተው ሐመር ችላው ምንድን ነው 
ኧረ ተው ዱሪ ችላው ምንድን ነው 
ሰይፍ ጦር ቢወረወር ለእኔም ለአንተም ነው አለ
ጀግናው !!! ጦር ቢወረወር ለእኔም ለአንተም ነው ያለ ከውጭ የሚመጣ ኃይል ኹሉ ኢትዮጵያውያንን አይመርጥም የሚጠቅመው ለኢትዮጵያ ሀገራችን ለኢትዮጵያዊነታችን በሃይማኖታችን አምነን ከእግዚአብሔር ጋር አንድ ሆነን ብንኖር ነው ።

ኢትዮጵያዊ ራሳችንን ቤተሰባችንን ማዳን ታሪካችንንም ለዘር ማስተላለፍ የምንችለውና ከዚህ አንጻር ነው መታገል ያለብን ።

እንግዲህ እኔ ብዙ ተናግርያለሁ ጊዜያችሁንም እንደወሰድኩ ይሰማኛል ምንአልባትም የልባችሁን ላይሆን ይችላል ቢሆንም እኔ መልእክት አስተላልፍ ያለኝን አስተላልፌያለው !!! በተቻለ መጠን እሺ የሚላችሁ ካገኛችሁ ተባብራችሁ ቤተክርስቲያንን ማዳን አይ ኹሉም  አንድ ዓይነት ከኾነባችሁ ጊዜያችሁን ጠብቁ ይሄ ቀርቶብን ይሄ እንዲህ ቢለን ከቤተክርስቲያን ልንባረር ነው  ወይ ? የት ልንሄድ ነው እኛ ? እስላም ልንኾን ነው ወይ ? እንዲህ  ልንኾን ነው ወይ ? እያሉ የሚያታልሏችሁን ትታችሁ  በያላችሁበት የጸሎት ሰዓት ወስናችሁ ጧትና ማታ ቢያንስ ቢያንስ ፲     ፲    ደቂቃ  ከሥራችሁ  አቋርጣችሁ  በእግዚአብሔር ፊት ቆማችሁ ስለሀገራችሁ ስለራሳችሁ ጸልዩ ይሄ ጾም አይለፋችሁ የምርኮ ዘመን ነው ! የምርት ዘመን ! እና አይለፋችሁ ተጠቀሙበት እግዚአብሔር በቸርነቱ ለፍጻሜ አብቅቶ በቸርነቱ እንደገና ያገናኘን  ።

ሰማዕት ዘዕንበለ ደም  ዳግማዊ ዲዮስቆሮስ ሊቀ ሊቃውንት አለቃ አያሌው ታምሩ የካቲት ፲፱፻፺ ዓ.ም በመኖሪያ ቤታቸው ካስተማሩት ትምህርት የተወሰደ
መጻእያቱን በትንቢት መነጽር አስቀድመው ያዩና መፍትሄውን በግልጥ ያስቀመጡ  እውነተኛ አባት በረከታቸው ትደርብን ጆሮ ያለው  መስማትን  ይስማ።

አለቃ አያሌው ታምሩ 

Share on Google Plus

ስለ የተለጠፈበት ቀን

    Blogger Comment
    Facebook Comment