በኢትዮጵያ፡ የግብፅ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን፡ ቅርንጫፍ በኾነችው፡ በዛሬዪቱ የኢትዮጵያ፡ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፥ ደግሞም፡ የእርሷ ተባባሪዎች በኾኑት፡ በቤተ ሕዝቧና በቤተ ምልክናዋ ዘንድ፡ በአኹኑ ጊዜ፡ በዚህ ረገድ፡ እየተፈጸመ ያለውን፡ እጅግ ተፃራሪና አስገራሚ ድርጊት፡ ለኪዳናውያንና ለኪዳናውያት የኢትዮጵያ ልጆች፥ ለሌሎችም ተመልካቾች፡ በግልጽ ማሳውቅ አስፈላጊ ኾኗል።
ለዚያውም፡ "ከመካከላቸው፡ አስተዋይና ተቈርቋሪ የኾነ፡ እውነተኛ ተመልካች ከተገኘ!" ማለት ነው፤ ይኸው ድርጊት፡ ከኢትዮጵያዊው ቀርቶ፡ ከሰብኣዊው ይሉኝታ እንኳ የተራቆተ፥ ወደር የሌለው፡ ሃይማኖታዊ ንቀትና ድፍረት የተመላበት መኾኑ፡ በገሃድ ሲታይና በግልጽ ሲታወቅ፡ አስገራሚነቱና ተፃራሪነቱ፡ የቱን ያህል የከፋ መኾኑ፡ በበለጠ ተጋልጦ ይገኛል። "ይህ ድርጊት፡ ምን ዓይነት ቢኾን ነው፡ ይህን የመሰለ ጥፉ መልክና ዐጉል ግምት ተሰጥቶት የቀረበው?" የሚል ጥያቄ፡ በአንባቢዎች ዘንድ ሊነሣሣ እንደሚችል ይታወቃል። ተገቢ ጥያቄ ነው። የዚህንም ጥያቄ ትክክለኛነት፡ ከዚህ የሚከተለው ሓተታ፡ በሚበቃ ያረጋግጠዋል።
ያ ድርጊት፡ ኹለቱም፡ ቅድስት ድንግል ማርያም በኾኑት፡ በእነዚያ፡ በርእሰ አድባራት ወገዳማት አኵስም ጽዮን ቤተ ክርስቲያን እና በአዲስ አበባው፡ "መንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ" የሰበካ ቤተ ክርስቲያን የክብር ስያሜ ላይ ሳይቀር፡ ማዋረጃ ቀንበር ኾኖ፡ በተጽዕኖና በተንኰል የተሠነቀረውን፡ እነርሱ፡ "CATHEDRAL (ካቴድራል)" የሚሉትን፡ ባዕድና ተፃራሪ እንግዳ ቃል ይመለከታል። "ባዕድና ተፃራሪ እንግዳ ቃል" የተባለውም፡ ካቶሊካውያንና በነገረ-መለኮት ቀኖናቸው፡ የካቶሊክን የመሰለ እምነት ያላቸው፡ የግሪክ ኦርቶዶክሳውያን፥ ግብፃውያኑ ኦርቶዶክሳውያን ጭምር የሚጠቀሙበት ስለኾነ ነው። ማንነታቸው፡ ከላይ የተገለጹት፥ "እነርሱ" የምንላቸው፡ የራሳችን ወገኖች፡ ይህን የመሰለውን ድርጊት የፈጸሙትና እየፈጸሙ ያሉት፡ በስንፍና ያላዋቂነት ስሕተት፥ ወይም፡ ኾን ብለው፡ በአዋቂነት ጥፋት መኾኑን ለይቶ ለመገንዘብ፡ ለማንም አስተዋይ ተመልካች፡ የሚያዳግተው አይደለም።
ከጥንት ጀምሮ፡ በኢትዮጵያ እና የኢትዮጵያ በኾነው ኹሉ ላይ፡ ከፀረ-ኢትዮጵያ ጎራ የሚታሰበውና የሚታቀደው፥ የሚነገረውና የሚካኼደው ተፃራሪ ድርጊት፡ ምን እንደኾነ፡ በማያጠራጥር ኹኔታ ይታወቃልና። አዎን! እነርሱ፡ "CATHEDRAL (ካቴድራል)" የሚሉት፡ ይኸው ባዕድና ተፃራሪ ቃል፡ ከግሪክኛ የተገኘ ሲኾን፡ የባዕዳኑ ባህልና አጠራር በኾነው ዘይቤ በመጠቀም፡ "የመነኵሴው PaPas (ጳጳስ) መቀመጫ ወንበር የሚገኝበት ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን" ተብሎ ይተረጐማል። ስለዚህ፡ አንድ ሃይማኖታዊ ድርጅት፥ በተለይም፡ ይኸው ሃይማኖታዊ ድርጅት፡ "ኢትዮጵያዊ ነኝ!" የሚለው ቤተ ክህነቱ ከኾነ፡ ባዕድና ተፃራሪ በኾነው፡ በዚህ፡ "CATHEDRAL (ካቴድራል)" በሚሉት ቃል በሚጠቀምበት ጊዜ፡ እጅግ በብርቱ ጥንቃቄን እንዲያደርግ ያስፈልገዋል፤ ይጠበቅበታል፤ ይገባዋልም። ምክንያቱም፡ ይህን ድርጊት፡ በሚፈጽምበት ጊዜ፡ ማለትም፡ በዚህ፡ "CATHEDRAL (ካቴድራል)" በሚሉት ቃል በሚጠቀምበት ጊዜ፡ ያ ሃይማኖታዊ ድርጅት፥ ወይም፡ ይኸው፡ "ኢትዮጵያዊ ነኝ!" የሚለው ቤተ ክህነት፡ "ካቶሊካዊ መኾኑን፡ በማያጠራጥርና በማያወላውል መልክና ይዘት፡ በውስጡ፡ ለራሱ፥ በውጭም፡ ለዓለሙ ጭምር፡ በይፋ ማረጋገጡ ነውና።
ይህ ድርጊት፡ በገሃድ ተከሥቶ መታየት የጀመረበትን፡ ቀደም ያለውን ኹኔታ፡ እዚህ ላይ፡ ባጭሩ ማውሳቱ፡ አግባብ ይኾናል። ይኸውም፡ በዚህ ረገድ፡ በድሮው ጊዜ፥ በተለይም፡ በአሕመድ ግራኝ ወረራ ምክንያት፡ በኢትዮጵያ ላይ የደረሰውን ጥቃት ለመቋቋም በሚል ሰበብ፡ ከፖርቱጋል የእርዳታ ጦር ሠራዊት ጋር፡ ሠርጎ የገባው የካቶሊካውያኑ ኢየሱሳውያን ተልእኮ፡ በአኹኑ ጊዜ፡ "CATHEDRAL (ካቴድራል)" የሚለውን ረቂቅ የወረራ ዓርማ አንግቦ፡ እነሆ፡ በይፋ ተግባር ላይ መዋል የጀመረበት ኹኔታ ነው። እርሱም፡ ያ፡ በባዕዳኑ ፀረ-ኢትዮጵያ ጎራ ሲውጠነጠን የኖረው ጥንሥሥ፡ ምንም እንኳ፡ በአጼ ሱስንዮስ ዘመን ፈንድቶ፡ መንግሥታዊ እውቅናንና ኃይልን ቢያገኝም፡ በልጁ፡ በአጼ ፋሲል ከተወገደ በኋላ፡ ሰንኮፉ ስላልተነቀለ፡ በየዘመናቱ እያመረቀዘ መቀጠሉ እንዳልቀረ ይታመናል።
ያም ኹኔታ፡ ለካቶሊካውያኑ ኢየሱሳውያን፡ ታማኝ መሣሪያቸው ኾነው ባገለገሏቸው፡ በአጼ ኃይለ-ሥላሴ ዘመን፡ እርሳቸው፡ ለራሳቸውና ለቤተሰባቸው መታሰቢያና መቃብር ይኾን ዘንድ ላሳነፁት፡ ለአዲስ አበባው ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን፡ የማዕርግና የክብር ስም ኾኖ በተሰጠው፡ "መንበረ ጸባኦት" በሚለው ቃል ላይ፡ ተደርቦ ብቻ ሳይኾን፡ "ቤተ ክርስቲያን" የሚለው ስያሜ ተነሥቶ፡ "CATHEDRAL (ካቴድራል)" የሚለው ካቶሊካዊው መታወቂያ እንዲተካ መደረጉ ነው። ይህም ድርጊት፡ እውን ኾኖ የተፈጸመው፡ በዚያን ጊዜ፡ በግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ገዳማት ሠልጥነው በተመለሱትና ይህንኑ ቤተ ክርስቲያን፡ በአስተዳዳሪነት ይመሩ በነበሩት፥ በመጨረሻም፡ በደርግ ዘመን፡ PaPas (ጳጳስ) በኾኑት፡ በመነኵሴው ሊቀ ሥልጣናት አባ ሀብተ ማርያም ወርቅነህ እንደነበረ ይታወቃል።
ታዲያ! በአኹኑ ጊዜ፡ በአገር ቤት ኾነ፥ በባዕዳን አህጉር ውስጥ የሚቋቋሙት የሰበካ አብያተ ክርስቲያናት ኹሉ፥ የቀድሞዎቹ ጭምር፥ በተለይም፡ ሕንፃቸው፡ ዘመናዊነትና ግዝፈት ያለው ኾኖ በሚገኝበት ጊዜ፡ በይበልጥ፡ የቤተ ሕዝቡ አባሎች የኾኑት፡ ምእመናንና ምእመናት፡ ያ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያናቸው፡ "CATHEDRAL (ካቴድራል)" የሚለውን፡ በእነርሱ ዘንድ፡ "እንደታላቅና ብርቅ ማዕርግ" የቆጠሩትን ስያሜ እንዲጎናጸፍላቸው፡ ከቤተ ክህነቱ የበላይ ባለሥልጣኖች፡ ፈቃዱን ለማግኘት፡ የሚያደርጉት ሽር ጉድ፥ የሚያቀርቡት ገጸ በረከትና የሚያካኺዱት ውጣ ውረድ፡ ለድርጊቱ አስገራሚነትና ተፃራሪነት፡ አንዱ ዓይነተኛው አስተዋጽኦ ኾኖ ይታያል። እነዚህ፡ የቤተ ሕዝቡ ወገኖች የኾኑት ምእመናንና ምእመናት፡ ይህን የመሰለውን ድርጊት፡ በሚያስተዛዝብ ኹኔታ የሚፈጽሙት፡ "CATHEDRAL (ካቴድራል)" የሚለውን፡ የቃሉን ካቶሊካዊነት፡ "ባለማወቅና በሞኝነት ነው!" እንዳይባል፡ በዚህ አንጻር፡ ስለቃሉ ካቶሊካዊነት፡ የቤተ ክህነቱ አባሎች የኾኑት ካህናቱ ብቻ ሳይኾኑ፡ እነርሱ፡ ምእመናኑና ምእመናቱ ጭምር፡ በትክክል የሚያውቁ መኾናቸውን፡ የሚያመለክቱ፡ አንዳንድ አሳማኝ ኹኔታዎች እንዳሉ መጠቆም ይቻላል። ከእነዚህም መካከል፡ አንዱ፡ ቀድሞ፡ በአዲስ አበባ የተሠራው፡ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን የሚገኘው፡ በብረት ሠረገላው (የምድር ባቡር) ጣቢያ አጠገብና በቸርችል ጎዳና ላይ ሲኾን፡ ሕዝቡ፡ ያን ቤተ ክርስቲያን የሚጠራውና በአድራሻነቱም የሚጠቀመው፡ "ቤተ ክርስቲያን" የሚለውን የወል ስም ሳይጨምር፡ "CATHEDRAL (ካቴድራል)" እያለ፥ የካቶሊክ የኾነውን ትምህርት ቤትም እንኳ የሚጠራው፡ "ካቴድራል ትምህርት ቤት" እያለ እንደኾነ ይታወቃል።
ከዚህ የተነሣ፡ "CATHEDRAL (ካቴድራል)" የሚለው ቃል፡ የካቶሊክ ብቻ በመኾኑ፡ የቃሉ መጠቀስ፡ ካቶሊካዊ መኾንን እንደሚያረጋግጥ፡ ሕዝቡ፡ በትክክል የማወቁ እውነታ፡ ከቶ የሚያጠራጥር አይደለም። እንግዴህ፡ እነርሱ፥ ኹሉም፡ ይህን እውነታ እያወቁ፡ የፈጸሙትና እየፈጸሙ ያሉት፡ ከላይ የተጠቀሰው፡ በባዕዳኑ ፀረ-ኢትዮጵያ ጎራ እየተካኼደ ያለው፡ የሴራ ድርጊት፡ ከዚህ እንደሚከተለው፡ ባጭር ዐረፍተ ነገር ተጠቃልሎ ቀርቧልና፡ አኹንም፡ አስተዋይ ተመልካች ካለ፡ ይየው!
በመጀመሪያ ደረጃ፡ የእነርሱ፡ ማለትም፡ በቤተ ክህነቱ ውስጥ፡ የቤተ ሕዝባቸው ወገኖች የኾኑት ምእመናንና ምእመናት፡ የቅዱሱ ኪዳን ኢትዮጵያዊነት ተዋሕዶ ሃይማኖት መታወቂያና መለያ የኾኑት፡ ርእሰ አድባራት ወገዳማት፥ "መንበረ ጸባኦት፥ ደብረ መዊዕ፥ ሓመረ ኖኅ፥ ደብረ ኃይል፥ መንበረ ፀሓይ፥ ደብረ ጽጌ፥ መንበረ መንግሥት፥ ደብረ ሣህል፥ ታዕካ ነገሥት፥ ደብረ ሰላም፥ መካነ ሕይወት፥ ደብረ አሚን፥ መካነ ሰማዕት፥ ደብረ ምሕረት፥ ምስካየ ኅዙናን፥ ደብረ ብሥራት፥ ..." እኒህንና እኒህን የመሰሉ የክብርና የማዕርግ ስሞች እንዳሉ ያውቃሉ።
ይህን አውቀው፡ እነዚህኑ የመሰሉ የክብርና የማዕርግ ስሞች ተመርምረውና ተጠንተው፥ ተመርጠውና ተፈቅደው፡ ለሕንፃ ቤተ ክርስቲያናቸው እንዲሰጥላቸው በመጠየቅ ፋንታ፥ እንዲያውም፡ እነዚህኑ የመሰሉ የማዕርግ ስሞች እያሏቸውም እንኳ ቢኾን፡ በእነዚያ ላይ፡ ይኸው "CATHEDRAL (ካቴድራል)" የሚለው ቃል፡ በተደራቢነት እንዲታከልላቸው፡ የቤተ ክህነቱ መሪዎች ለኾኑት፡ ለዘመኑ መነኰሳት፡ ከከፍተኛ ገጸ በረከት ጋር፡ ልመናንና አቤቱታን በማቅረብ፡ ያን ያህል የጭንቅ ጥብ ውጣ-ውረድ እንዲያካኺዱ ይደረጋል።
በኹለተኛ ደረጃ፡ እኒሁ፡ የቤተ ክህነቱ መሪዎች የኾኑት፡ የዘመኑ መነኰሳት፡ ከቤተ ሕዝቡ የቀረበላቸውን ይህን ጥያቄ፥ ልመናና አቤቱታ፡ ከተገቢው ገጸ በረከት ጋር ተቀብለውና አጽድቀው፡ ፈቃዱን እንዲሰጧቸው ይደረጋል።
በሦስተኛውና በመጨረሻው ደረጃ፡ ቤተ ምልክናው፡ ያን የቤተ ክህነቱን ፈቃድ፡ በሕጋዊነት እንዲያጸናው ይደረጋል። ታዲያ፡ በዚህ ድርጊት፡ ራሷን፡ "የኢትዮጵያ፡ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን" ብላ የምትጠራው፡ የዛሬዪቱ ቤተ ክህነት፥ የእርሷ ተባባሪዎች የኾኑት፡ ቤተ ሕዝቧና ቤተ ምልክናዋ ጭምር፡ በኢትዮጵያ፡ የግብፅ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን፡ ቅርንጫፍ መኾናቸው ብቻ ሳይኾን፡ "ካቶሊክም ኾነናል!" ማለታቸው አይደለምን? አዎን! ነው እንጂ። እንዲህ ከኾነ፡ ኹሉም፡ ይህን ሲያደርጉ፡ "አዎን! እኛ፡ ካቶሊካውያንና ካቶሊካውያት መኾናችንን፡ እናንተም፡ ለራሳችሁ፥ ለእኛም፡ ለእየራሳችን አረጋግጣችሁ፥ ለዓለሙ ኹሉ ደግሞ፡ በይፋ አሳውቁልን!" ማለታቸው መኾኑን፡ ሊዘነጉት አይገባቸውም። በኢትዮጵያ፡ የእግዚአብሔር መንግሥት ዘንድ ግን፡ ይህ ድርጊት፡ ተቀባይነት የለውም።
ከሌሎቹ፡ የዓለም ሃይማኖቶችና አብያተ ክርስቲያናት ኹሉ ተለይታ፡ የአያሌ ሽህ ዓመታት ቅድሚያ ላላት፥ ይልቁንም፡ የ፯ሺ፭፻፱ ዓመታት ዕድሜ ባለጸጋ ከመኾኗ የተነሣ፡ ጥንታዊትና አረጋዊት ለኾነችው፥ ራሷም፡ መንበረ ጸባኦት፥ ቅድስት ሥላሴና ኢትዮጵያ፥ የእግዚአብሔር መንግሥት፥ የቅዱሱ ኪዳን ተዋሕዶ ሃይማኖትም በኾነችው፡ በቅድስት ድንግል ማርያም፡ መለኮታዊ መለያና መታወቂያ ሕያው ስም ላይ፡ ምንም ዓይነት፡ ሌላ ቅጥያና ባዕድ የኾነ፡ የክብርና የማዕርግ ስም አያስፈልጋትም። "Orthodox" (ኦርቶዶክስ)፥ "CATHEDRAL" (ካቴድራል)" የሚለው ጭምር።
Blogger Comment
Facebook Comment