ከዲያቆን ብዙነህ ወልዴ
በእኛ ኢትዮጽያውያን ዘንድ ለውድቅታችን እና ለስንፍናችን ምክንያት ስናደርግ ጣታችንን ሌላው ላይ እንቀስራለን። ተማሪ መምህሩ ላይ፤ መምህሩ ትምህርቱ ላይ፤ ትምህርቱ ተማሪው ላይ፤ ህዝብ መንግስት ላይ መንግስት ቡድኖች ላይ፤ ሰራተኛው አለቃው ላይ፤ አለቃው ሰራተኛው ላይ... ብቻ ሁሉም ለጥፋት እና ለወቀሳ ጊዜ እጁን የሚቀስርበት አካል ብዛቱ!!
ዓለማችን ላይ ያለው እያንዳንዱ ነገር እርስበርሱ የተሰናሰለ ነው። አንዱ አንዱ ላይ የተጠላለፈ ነው። ማንም ፍጹም ባለመሆኑ አንዱ ያጠፋው ለ አንዱ ይተርፋል የአንዳችን ጥፋት ለሌላው የሩሮ መመሰቃቀል ምክንያት ሊሆን ይችላል። ኑሮው የተመሰቃቀለበት ግን ሙሉ ለሙሉ አጥፊው ላይ ጣቱን መቀሰር የለበትም። እራሱንም ማየት እና መመልከት አለበት። ያኔ ምናልባት አብዛኛውን ጥፋት እራሱ ጋር ሊያገኘው ይችላል።
ይህ የሰዶ ማላከክ ባህሪ ከየትኛውም ቦታ እና ተቋም በላይ በቤተ ክርስቲያናችን ጎልቶ ይታያል። ለቤተ ክርስቲያኒቱ እያንዳንዱ እንቅፋት እና መሰናክል ጣታችንን ሌላው ላይ እንቀስራለን። ያለውን ችግር ተባብሮ እንደማጥፋት ጊዜያችንን በመወቃቀስ እና በ ሐሜት እንጨርሳለን። በእያንዳንዱ የግል መንፈሳዊ ህይወታችን ላጋጠሙን ችግሮችና መንፈሳዊ እድገታችን ላለማደጉ ቤተክርስቲያንን እና የቤተክርስቲያንን አገልጋዮች ተጠያቂ እናረጋለን።አገልጋዮችም በሌሎች አገልጋዮችና በትላልቅ አባቶች ላይ፤ አባቶች ደግሞ ምዕመን እና መንግስት ላይ። ብቻ መፍትሄው ሳይሆን ሽኩቻውና ትንቅንቁ ብዙ ነው።
ቤተ ክርስቲያን እራሷን የቻለች አካል ነች። በምስጢራዊ እና መለኮታዊ አገላለጽ መግለጹን ትተን ውስጧ ከቅዱስ ሲኖዶስ አባቶች ጀምሮ በየደረጃው የካህናትና አገልጋዮች እንዲሁም የምዕመናኑን አንድነት የያዘች ነች። ቤተ ክርስቲያኒቷ እራሷን የቻለች አካል(entity) ስለሆነች የራሷን አቋም ማራመድ እና የራሷን ውሳኔ መወሰን ትችላለች። ይሄም የምታረገው ነገር ቤተ ክርስቲያኒቱ እንዳደረገችው ይቆጠራል። ይህም መልካሙንም ሆነ መጥፎውን ይመለከታል። ለምሳሌ:- ቤተ ክርስቲያኒቱ ለምታቋቁማቸው ምግባረ ሰናይ እና ህብረተሰባዊ አገልግሎቶች ፧ አረጋውያን መርጃ፣የህክምና ተቋማት፣ ት/ቤቶች፣ ወዘተ… የቤተክርስቲያኒቱን ስም በመልካም ያስነሳሉ፤ ብሎም በአስተዳደራዊ ጉዳዮች መካከል መንግስታትን ልታስማማና ጦርነትን ልታስቆምም ትችላለች። በሃያኛው መክዘ መጀመሪያዎቹ እንደ ነበረችው የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ደግሞ መሳሪያቸውን ባርካ ጦርነት ከጋበዘችም የቤተ ክርስቲያኒቱን ስም በአሉታ ሊያስነሳ ይችላል፤ ከዛም አልፋ የመስቀል ጦርነት ልታውጅ ከቻለችም ለሚደርሰው እያንዳንዱ ትርፍ እና ኪሳራ ቤተ ክርስቲያኗ ተጠያቂ ትሆናለች።
በሌላ በኩል ቤተ ክርስቲያኒቱ አቅፋ የያዘቻቸው ካህናትና ምዕመናን ለሰሩት አሉታዊ ሥራ ቤተ ክርስቲያኒቱን መውቀስ ተገቢ አይደለም። ምናልባት ያንን ሥራ እንዲሰሩ ትእዛዝ አስተላልፋና ደንግጋ ከሆነ ሊያስጠይቃት ይችላል። ከዛ አልፎ ደግሞ አብዛኛው ካህናት ያልተገባ ተግባር ሲያከናውኑ የቤተ ክርስቲያኒቱን ስም ሊያስጎድፉ ይችላሉ። ምዕመኑም ልቅ ከወጣ እና ከሃይማኖት ውጪ የሆነ ህይወት መኖር ከጀመረ ቤተ ክርስቲያኒቱን ሐዋርያዊ ተልዕኮ ጥያቄ ውስጥ ሊከተው ይችላል።
አሁን ያለውን ወቅታዊ ሀገራዊ ሁኔታ ስንመለከት ብዙ ነገር ግራ ያጋባን ይመስላል። ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያለው ብክነትና መዝረክረክ እንዲሁም ከመንፈሳዊ ግልጋሎት በላይ ለንዋይ መንቀሳቀሳቸው ብዙ ጥያቄን ይጭራል። ምዕመኑም የተማረውን ትምህርት ባልሰማ እያለፈ ከሚከተለው የክርስቶስ አስተምሮ በተቃራኒው በኃጢአት ተዘፍቆ በዘር ተከፋፍሎ ወንድም በወንድሙ ላይ እየተነሳ ሲታይ አረ መንገድን የሚያቀና የአባቶች ተግሳጽ የት ገባ ያስብላል።
ስለ ሐዋርያዊ ተልዕኮ እዚሁ እትም ላይ ከወንድሞቼ ጽሑፎች መገንዝብ ትችላላችሁ። በሌላ እትምም እንመለስበታለን። ከኔጋ ስለ ምዕመኑ ሐዋርያዊ ተልዕኮን አለመከተል እና ከቤተ ክርስቲያን መራቅ አንድ አንድ ነገር እንበል።
ለቤተ ክርስቲያናችን እንደ ካህናት አባቶች መጥፋት፣ የካህናት ቁጥር ማነስ፣ የንዋየ-ቅዱሳን እጥረት በላይ የምዕመኖቿ ከቁጥር መቀነስ ትልቅ ፈተና ነው፤ የቤቱ አንድ አካል ናቸውና። ከቁጥር ቀነሱም ማለት የነገው እጣፈንታቸው መንገድ ዳር እንደተዘራ ዘር ቃሉን ክደው፤ ተመልሰው ቤተክርስቲያኒቱን ወጊ መሆን ነው ፤ በስተመጨረሻም የገሃነብ ፍርደኞች መሆን። ስለዚህ የ እያንዳንዱ ምዕመን መጥፋት ሁላችንንም ሊያሳስበን ይገባል።
በአሁኑ ጊዜ ቤተ ክርስቲያኒቱ ያላት የአማኝ ቁጥር ከሃገሪቱ ህዝብ ቁጥር ክፍተኛውን ቦታ ይይዛል፤ ከጊዜ ወደጊዜ ግን ይህ ቁጥር በጣም እየቀነሰ መጥቷል። የቀነሰው እምነቱን ለቀው ክደው በመሄድ ብቻም አይደለም፤ በቅዱስ ቤቱ ተገኝቶ ቃሉን የሚሰማ፣ ታቦታቱን በእልልታ አጅቦ የሚያነግስ፣ ለማህበር ፀሎት የሚተጋ፣ ቅዱስ ስጋውንና ክቡር ደሙን የሚቀበል፣ ንሰሃ ገብቶ ተግሳፅና ምክርን የሚቀበል፣ በአጠቃላይ ለቤተ ክርስቲያኒቱ አንድነት የሚቆረቆር ምዕመን በቁጥር በጣም በሚባል ሁኔታ እያጣን ነው። አብዛኛው ምዕመን ደግሞ ለምስጢር የቀረበ ከአገልግሎት የራቀ፣ በእውቀት የመጠቀ በምግባር ግን የዘቀጠ፣ የቤቱ ክብር የገባው የቤቱን ክብር ግን ያላስከበረ፣ ስለ ንሰሃ የገባው ንሰሃ ግን የማይገባ፣ ስለ እንድነት እና አንዲት ቤተክርስቲያን የተማረ በአንድ ልብ እና በህብረት ግን የማይጸልይ፣ በአጠቃላይ ወደቤቱ ብዙም ያልቀረቡ ከቤቱም ብዙ ያልሸሹ መሐል ሰፋሪዎች ሆነዋል። ወይ ያልሞቁ ወይ ያልቀዘቀዙ ለብ ያሉ!
አብዛኛዎቹ ብዙም አትቅረብ ብዙም አትራቅ አባዜ የተጠናውታቸው ለምን እንደራቁ ሲጠየቁ የሚያቀርቡት መልስ ከላይ ከመግቢያችን ላይ እንደዘረዘርነው ጣትን ሌላ ላይ መጠቆም ነው።
“ቤቱን ገንዘብ መሰብሰቢያ እና መለመኛ አድርገውት እንዴት እንምጣ፣ የንግድ ቤት አረጉት፣ አስተዳዳሪዎቿና ባለስልጣኖቿ በሙስና ተጨማልቀው፣ ዘረኝነት እያየንባት እንዴት ብለን፣ ሌባ በዝቶባት፣ የምንግስት እና የፖለቲካ አሸርጋጆች በዝተው፣ ከእግዚአብሄር ቃል በላይ እርስ በራስ በከንቱ ውዳሴ ሰዓቱን እየገደሉት፣ ሰካራም ካህን እያየሁ….” ብቻ ብዙ ብዙ የጣት መጠቆሚያ ቃላትን ይሰነዝራሉ።
ሰው ለማወቅም አውቆ ለመቅረብም፣ ለመራቅም ነጻ ምርጫ አለው። ነጻ ምርጫ ማለት እግዚአብሄር አምላክ ለሰው ልጅ በሥነ ፍጥረት ጊዜ የሰጠው ሃብት ነው። ይኸውም የወደደውን እንዲሰራ የጠላውን እንዲተው የሚያደርግ ነው። የእግዚአብሄርን ቃል አውቆ አለመጠቀምም ደግሞ የራሱ ፍርድ አለው። ያላበዛናትን እና ያልተጠቀምናትን መክሊት እንደቀበርናት ይቆጠራልና። እስኪ የቃሉን ታላቅነት ከተረዳህ እንዴት ሰንሰለቱንና ቀሳሪ ጣታችንን ወደጎን ትተን እንደምንጓዝ እንነጋገር፦
አ - መልካም መሬት ሁን
አንተ ጣትህን የቀሰርክባቸው ካህናት ያንተ እረኞች፣ ጠባቂዎች የቃሉ ገበሬዎች ናቸው። እነሱ ዘሩን የሚዘሩ ገበሬዎች ናቸው፤ ዘሩ የእግዚአብሄር ቃል ነው፤ የእርሻው መሬት ደግሞ አንተ ነህ። ዘሩ ሰላሳና መቶ እጥፍ እንዲያፈራ አንተ መልካም መሬት መሆን አለብህ። ስለገበሬው አታስብ ስለ አንተ ነፃ አእምሮ ብቻ አስብ። አንተ ማመዛዘን እንድትችል ሆነህ አውቀሃልና እነሱን ጥፋተኛ አታርግ። እነርሱንም አትፍረድባቸው፤ ፍርድ የእግዚአብሄር ብቻ ነው። እነሱ ካጠፉ የሚቀጣበት የራሱ መዝገብ አለውና። አንተ ከቃሉ በላይ የገብሬውን መንገድ ከተከተልክ መንገድ ላይ እንደተዘራ ዘር ልብህ ለዲያቢሎስ ይጋለጣል። (ሉቃ 8፥5-15) አንተ ልብህን መልካም ካረከው ተለይተህ በቃሉ ታፈራለህ። መልካም ልብ እንደምን ያለ ነው፦
ንፁህ ህሊና ያለው
ዘር የሚዘራበት መሬት ከእሾህና ከቁጥቋጦ ንጹህ መሆን እንዳለበት ሁሉ ህሊናችንንም በኃጥያት ሳናቆሽሽና ሳናጨልም በንፅህና መያዝ አለብን። በፆምና ጸሎት ማጽናትና ማንቃት አልብን። እንዲሁም በየጊዜው ንሰሃ መግባት ቅዱስ ስጋውን ክቡር ደሙን መቀበል አለብን።
ትህትና የተላበሰ
ትህትና ማለት በአጭሩ እራስን ዝቅ ማድረግ ነው። እኛ ክርስቲያኖች ትልቁ የትህትና መምህራችን ክርስቶስ ነው። እሱ ታላቅ ሆኖ ሳለ የኛን ሰውነት ተዋሃደ። እምላክ ሆኖ ሳለ ዝቅ ብሎ የፍጡሩን እግር አጠበ። ኩራትና መታበይን ማሳየት የተሰጠንንም ያሳጣናል። አወራረዳችንም የከፋ ይሆናል።
መልዓኩ ቅዱስ ገብርኤል ለድንግል ማርያም የአምላክ እናት እንደምትሆን በነገራት ጊዜ
“እነሆኝ የእግዚአብሄር ባርያ እንደቃልህ ይሁንልኝ”(ሉቃ 1፥38)
አለች እንጂ አልታበየችም። አንተም ባለህ ነገር አትኩራ አትመጻደቅ። በትህትና ቃሉን ተቀበል ዝቅ ብለህ ቃሉን ስማ ያኔ የቃሉ ታላቅነት ይጋባሃል ስልሳና መቶም ታፈራለህ።
ቡ - ባለህ ጥበብ ተጠቀም
ማንኛውም ሰው እራሱንና በዙሪያው ያሉትን ነገሮች ለመመርመርና ለመገንዘብ ጥበበኛ ሆኖ መገኘት አለበት።ቅዱስ ጳውሎስም “በጥበብ ሂዱ” እንዳለ (ቆላ 4፥16)።በብልሃትና በጥበብ ካልተንቀሳቀስን እንደ ገለባ ቀለንና ነፍሰን ልንገኝ እንችላለን። አንተም በቤተ ክርስቲያኒቱ ያሉትን ችግሮች እያየህ ወደኃላ ከምታፈገፍግ በጥበብ ፍታቸው ገበናዋንም ሸፍንላት። ያንተ መሸሽ ፍርሃትን እንጂ ያለህን ቅንአት አያሳይም ለቤቱ ቅንአት ካለህ ያለባትን ችግር ፍታላት ታገልላት። ባልህ ችሎታ አስተዳደራዊ መዋቅሯን አግዝ፤ የተዝረከረከውን ሰብስብላት። ይህን ተንተርሰው ሊያጠፏት የመጡትን የመናፍቃን ወታደሮች በወንጌል ጋሻ መክተህ በጎቿን እና ቅጥሯን ጠብቅላት። ድፍረት በተሞላበት ሳይሆን ጥበብ በታከለበት ብልሃት ናታኒም ሆነህ ደጇን ጥረግላት አትሽሻት።
ጊ - ስለ ጽናት ታውቃለህ?
ጽኑዕ ማለት ብርቱ ሰርቶ የማይደክም የማይሰላች በአመነበት እምነት የሚጸና በተሰራለት ሥርአት የሚኖር በመከራ የማይለወጥ ማለት ነው። ክርስቲያን ስለሆንን የምንፈራውና ወደኃላ የሚያሸሸን ምንም ነገር የለም። ፍርሃት የጽናት ተቃራኒ ነው፤ ስንፈራ ሽብር ተስፋ መቁረጥና ማመንታት ይከተሉናል፡ እነዚህ ደግሞ ክርስትናችንን ወደኃላ ይጎትታሉ ከቤቱ ያሸሹናል። የሚድነው እስከ መጨረሻይቱ ህቅታ የታገሰ እና የጸና እስከሆነ ድረስ በጽናት የቤቱን ችግር አስተካክል። የቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ምን አገባኝ አይመለከተኝም አትበል። ቤተ ክርስቲያን ምቹ ሲሆን የምትሄድበት ምቾት ሲርቃት የምትርቃት ቤት አይደለችም። ያጋጠማት ችግር ፈተና ነው፤ በፈተናዋ ጊዜ ከሸሸሃት ያንተ ጽናት የምቾት ነበር ማለት ንው። ስለዚህ ወንድሜ ለቤተክርስቲያን ክብርና ለመንፈሳዊ ህይወትህ ጽኑዕ ተጋድሎህ መቼም እንዳይለይህ።
ዳ - ለአንድነት አድላ
ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያናችን ከሌሎች የእምነት ተቋማት የተለየ የአንድነት እና የማህበር ባህሪ አላት። አብዛኛው ጸሎቷ በግል ህይወት ላይ ብቻ ሳይሆን ለሀገር፣ ለምእመኑ ህብረት፣ለ አንድነት፣ለ ማህበረ ካህናቱ.. ወዘተ የምትጸልይ ቤተ እምነት ነች። እንዳንድ ጉድፍ እያየህ ከማህበር ጸሎት አትቅር። የምህበር ጸሎት አንዱ የክርስቲያን ግዴታ ነው። በ ማህበርና አንድነት አመስግን፣ ጸልይ፣ አስቀድስ፣ ካህናት ሲያስተምሩ ከደጁ ተገኝተህ ቃሉን ተመገብ፣ የራስህና ምስጢር የሆነውን ነገር በግልህ ጸልይ ለራስህም የጥሞና ጊዜ ስጠው።
ሄ - ስለ ቤተ ክርስቲያኒቱ አንድነት እና በህይወት ስላሉት ካህናት ጸልይ
ቤተ ክርስቲያናችንን የሚመሯት በአካለ ስጋ ያሉ አባቶች አሏት፤ እነዚህ አባቶች ፍጹም አይደሉም ቅዱሳንም አይባሉም። በህይወት እያሉ ሃሳባቸውን ቀይረው የእግዚአብሄርን ህልውና የመካድ ሙሉ ነጻነት አላቸው። በህይወት እያለ ሃሳቡን የሚቀይር አለና አንተም እነሱ በወደቁና ድካማቸውን ባየህ ጊዜ አትዘናጋ ወደኃላ አትመለስ ከቤቱ አትሽሽ፤ ክህደት የታከለበት ትምህርት ከጀመሩም በአነጋገር ለዛቸው እና ዝናቸው ተማርከህ አብረሃቸው አትጓዝ፤ ይልቁንም አባቶች እንዳስተማሩን ስለ ቤተ ክርስቲያኒቱ አንድነት ጸልይ፣ “አባቶቿን ሊቃነ ጳጳሳት፣ጳጳሳት፣ ኤጲስ ቆጶሳት ቀሳውስት ካህናቶች ዲያያቆናት፣ መነኮሳት፣ሊቃውንት፣ዘማርያኑን፣ ሁሉንም የቤተ ክርስቲያኒቱ አገልጋዮች ፍቃዱ ሆኖ በህይወት ያቆያቸው ዘንድ፣በ አንዲት ሃይማኖት ያጸናቸው ዘንድ፣ በእኩልነት ያገለግሉ ዘንድ፣ መልካም እረኛ እንዲሆኑ ማስተዋሉን ያድላቸው ዘንድ ጸልይላቸው። ስለ ቤተ ክርስቲያኒቱ አንድነት፣ስለ ሃገር መሪዎች፣ ስለ ሀገራችን ሰላም ጸልይ።
ው - ማህበራዊ እና ሃገራዊ በጎ ክንውኖች ላይ በቤተ ክርስቲያኒቱ በኩል ንቁ ተሳትፎን አድርግ
ክርስትናዊ ከሆነው ተግባር አንደኛው ለሰው ልጅ በጎ ተግባራትን በፈቃደኝነት ለበልባዊ ፍቅር ማከናወን ነው። ሃይማኖት እና ዘርን ሳትለይ ሰው ለሆነው ሁሉ በጎ ለማድረግ የፈጠንክ ሁን። አባቶች ዝም ብለዋል ብለህ አንተም እጅህን አትጠፍ። በቤተክርስቲያኒቱ ስም ሆስፒታሎች፣ መንገዶች፣ ት/ቤቶች፣ ለምንዱባን መጠለያ፣ ባጠቃላይ ለገቢ ምንጭ ሳይሆን ለህሊናህ እረፍትና ለሃይማኖትህ ክብር ስትል ባማህበር አስገንባ። ከክርስትናዊ ወንድም እህቶችህ ጋር የታረዙትን አልብስ፣ የተራቡትን አብላ፣ ባጠቃላይ በበጎ ነገር ቤተክርስቲያንን አግዛት።
ዞ- በአጠቃላይ አንተ የራስህን ጎን በሚገባ ገንባ ከዛ በኃላ የተጣመመው መንገድ ይታይሃል፤ የተጣመመውን መንገድ እያቃናህ ጎባጣውን እያስተካከልክ ወደ ቅዱስ ቤቱ በአንድነት ተጓዝ፤
ጉዟችንን እስከፍጻሜው ያሳምረው!!

Blogger Comment
Facebook Comment