አንዳንድ ወገኖች ሙስሊም ታሪክ ጸሐፊዎች ለምን ሐሰት ይናገራሉ..? ምን አገኝ ብለውስ ያልሆነ ነገር ይጽፋሉ..? ብለው ይጠይቁ ይሆናል፡፡ መልሱ ቀላል ነው፡፡ የእስልምናን ኃይልና ተፅዕኖ ለማሳየት እንደሆነ ግልፅ ነው፡፡ በእስልምና አስተምሕሮ ውስጥ “ተቂያ” የሚባል የታወቀ አሰራር አለ፡፡ ይህም “የተፈቀደ ውሸት” ማለት ሲሆን በአንዳንድ ጉዳዮችና ሁኔታዎች ሊፈፀም የሚችል ነው፡፡ ለእስልምና ብሎ መዋሸት ደግሞ በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ የሚታይ ነው፡፡ የዚህ ታሪክ ዋንኛ ምንጭ የሆነው ኢብን-ኢስሐቅ እንዴት ያለ የማይታመን ሰው እንደሆነ በዝርዝር ተመልክተናል፡፡ ይህ ዓይነቱ አሰራር ግን በዚህ ብቻ የተገደበ አይደለም፡፡
ለምሳሌ በቁሳይ አምራ (Qusai Amra) ሶሪያ በሚገኘው የአል-ወሊድ (Al-Walid) ቤተመንግሥት (705-715) ላይ የተሳለውንና ለእስልምና የገበሩ መሪዎችን የሚያሳየውን ሥዕል መመልከት ይቻላል፡፡ “ለእስልምና ገብረዋል” ከተባሉት ነገሥታት መካከል አንዱ የእኛው ንጉሥ አድርአዝ ወይም ንጉሥ አርማህ ነው፡፡¹ ነገር ግን ይህ ታሪክ መሠረተ ቢስ እንደሆነ እራሳቸው ሙስሊም ጸሐፊያን የመሠከሩት ነው፡፡
ሀገራችን መቼም ቢሆን ለእስልምና እጅ የሰጠችበት የታሪክ አጋጣሚ የለም፡፡ አዲሱ ሃይማኖት በአረብ ባሕረ ሰላጤ የሚገኙ ሕዝቦችን ልብ ለመሳብ እንዲህ ያሉ የሀሠት ዜናዎችንና ድሎችን የመንገርና የማስነገር ዘዴ ይጠቀም እንደነበር መገንዘብ ይቻላል፡፡ ኢትዮጵያዊው ክርስቲያን ንጉሥ ሠልሞ እንደነበር መፃፍም የዚሁ ሥልት አካል ነው፡፡
የእስልምና ዋንኛው “ቅዱስ” መጽሐፍ የሆነውን ቁርአንንም ብንመለከት ባልነበረበት ዘመን የተፈፀሙ ታሪኮችን ጠምዝዞ የማቅረብ ባሕል አለው፡፡ ቁርአኑ ጥንታውያን አባቶችን በሙሉ ሙስሊም እንደነበሩ ይተርካል፡፡ የአይሁዳዊነት እምነትን መሥራች የነበረውን ሙሴን፣ ታላቁ አብርሃምን፣ ንጉሱ ዳዊትንና ነብያቱን ሁሉ ሙስሊሞች ናቸው ይለናል፡፡
ሌላው ቀርቶ እነርሱ “ኢሣ” የሚሉትን ኢየሱስንና ደቀመዛሙርቱን ሳይቀሩ እስልምናን የሰበኩ ሙስሊሞች መሆናቸውን ያውጃል፡፡ የዚህ ምክንያቱ በኋላ የመጣውን እስልምና ጥንታዊ መሠረት ለማስያዝ የተደረገ መላ እንጂ አንዳች እውነትነትም ሆነ ሽራፊ መረጃ እንደሌለው ይታወቃል፡፡ የመጽሐፉ ተማሪዎች ይህን አብነት አድርገው በታሪክ ውስጥ ያልተፈፀሙ ነገሮችን እንደተፈፀሙ አድርገው ቢፅፉ ብዙም አስገራሚ አይሆንም፡፡
የወደፊቱን ለመተለም የኋላ ታሪክ አስፈላጊ እንደሆነ ብዙ ምሑራን ይስማማሉ። ይህም የሳንኮፋ ትክክለኛ ትርጉምና ሂደት እንደሆነ መግቢያው ላይ ተመልክተናል። ግብ አድርገው ያሰቡት ነገር ላይ ተስፈንጥሮም ሆነ ተጉዞ ለመድረስ ታሪክ ጥሩ መንደርደሪያ ይሆናል። ቢሆንም ያለፈ ታሪክ በመረጃ የሚደረስበት እውነት እንጂ የአሁኑ ትውልድ እንደፈለገ የሚበይነው አይደለም፡፡ እንዲያ ከሆነ አጠቃላይ የፍለጋ ሂደቱን የመጥለፍ፣ የማዛባትና የማሰናከል እኩይ ተግባር ይሆናል። ሰንኮፍ ስንል የጠቀስነውም ይህንኑ አሉታዊ ኃይል ነው። በዚህ ኃይል እውነት እንዳይዛባና እንዳይድበሰበስ በዝርዝር በተመለከትነው ርዕስ ውስጥ ሰንኮፉን ከሳንኮፋው ማለትም ከታሪካዊው እውነታ የመነጠልና የማጥራት ሥራ በመጠኑ ተሠርቷል።
ታሪክን በመረጃና በታማኝነት የሚፅፉ ታሪክ ጸሐፊዎች የመኖራቸውን ያህል አንዳንድ ኃይላት ደግሞ ለሰነቁት የጥፋት ሥራ ታሪካዊ መነሻ ለማድረግ ሲሉ ያልነበሩ ታሪኮችን በመፍጠር የጥንቱ ዘመን ውስጥ ይዶላሉ፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ እጅግ የረዘመ ሐገረ መንግሥት ባላቸውና የጥንታዊነታቸውን ያህል በቂ የተፃፈ ታሪክ በሌላቸው ሀገራት ላይ ገብቼ ልፈትፍት ባዩ ብዙ ነው፡፡ በራሳቸው የእይታ መጠንና መሥፈርት አንዳንዶቹም በሰነቁት ሥውር ተልዕኮ ምክንያት የተዛባ መረጃ በታሪክ ስም ሊሠራጭ ይችላል፡፡ ይህንኑ አስመልክቶ የቤተክርስቲያን ታሪክ ጸሐፊና መምሕሩ ግርማ ባቱ የሚከተለውን ይላል
“የድርጊትን እውነታ በተለያየ ፍላጎት የተዛባ ትርጉም እየሰጡ የሚፅፉ አሉ፡፡ ጥናትና ጥረት የሚጠይቀውን በመላ ምት የሚፈጥሩ፣ በሩቅ ቆመው የሚበይኑ፣ በማያውቁት የሚፈርዱ፣ የተመቻቸውን ሃሳብ ለማስረፅ ድንጋይ የሚፈነቅሉና ነባራዊውን ታሪክ በማጣጣልና በማፍረስ የሚሠሩ እጅግ ብዙ ናቸው። የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያንና የኢትዮጵያ ታሪክ የዚህ ደባ ሰለባዎች ናቸው” ²
ነገሮች በጥንቃቄና መልከ ብዙ በሆነ መነጽር ከተቃኙ እውነታው ላይ አሊያም ወደዚያው የሚያቀርብ ድምዳሜ ላይ ያደርሳሉ። ሙስሊሞች “ነጃሺ” ሲሉ የሚጠሩት ኢትዮጵያዊው ክርስቲያናዊ ንጉሥ እንደሰለመ ደጋግመው ከሚፅፉት መጻሕፍት ጎን ለጎን ይጠና ዘንድ ያለመስለሙንና ለመስለምም የሚያበቃ አሳማኝ ምክንያት እንደሌለ ለማመልከት ይቺን አነስተኛ መጣጥፍ እነሆኝ ብለናል፡፡ ውድድርና ፉክክር ሳይሆን እውነትን በፍቅር ለሚፈልጉ ሁሉ ተጨማሪ ማንፀሪያ እንደሚሆን ተሥፋ አደርጋለሁ፡፡
ማጣቀሻዎች
¹ ኤፍሬም እሸቴ - አክራሪ እስልምና በኢትዮጵያ ገጽ፡22-23
² ግርማ ባቱ - የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ታሪክ - ከጥንት እስከ 6ኛው ክ/ዘመን -2014
ዓ.ም ገጽ፡17
(የሳንኮፋ ሰንኮፍ እና ሌሎች ከገጽ 125-127)
🔹የማጠቃለያውን ማጠቃለያ ስለእዚሁ ንጉሥና ርዕሰ ጉዳይ የምታነሳ ግጥም አድርገን ብናሳርግስ
አርማህ
በአብርሃ አጽብሃ ዙፋን በካሌብ ወንበር ተቀማጭ
ብርቱ መጠጊያ ለመሆን በስዱዳን ልብ ተመራጭ
ፍሬው በግልጥ የሚታይ የሆነ የወንጌል ማሳ
በጎነት ስሙን ያስጠፋው ያስከተለበት አበሳ
ፍትሕን በርትዕ ተርጉሞ
የከሳሽን አፍ ለጉሞ
ለተንከራታች ነፍሳት በሆነ ማረፊያ ወደብ
እምነት ምግባሩ ታብሎ በእንዲህ ያለ ልክ መሰደብ
ልክበር ባይ ታሪክ ሰርቄ
ቢጠብሰው በነገር ቃንቄ
የሐሠት ከል ቢለቀልቁት ብርሃኑ ለማይደበዝዝ
የሐቅ ጉልበቱ ጽኑ በዘመን ለማይደነግዝ
እውነቱን በብረት እርሳስ
እምነቱን በተግባር ክርታስ
ቀርፆ ላኖረ ጎበዝ
ስምከ አርማሕ ወ አድርአዝ
ለማይጠፋ ስም ላለህ ስምህ በከንቱ ለጠፋ
ሐሳዊ ብዕር በዕብለት የሐቅ ድንበርህን ቢገፋ
የአድማስ ድንጋይ ነው ልክህ ከሥፍራው አይናወጥም
በማዕበል ወጀቡ ብዛት ሕላዌው አይለወጥም
ምን ቢንጠራሩ አባዮች የክብርህ ጥጋት አይደርሱም
ስምህ በክታብ ይዘከር ጃንሆይ ንጉሠ አክሱም..!!!
Blogger Comment
Facebook Comment