ከትውልድ ማን አስተዋለ

✍ ቲና በቀለ | ኢትዮጵያ አውታር             

ከዘመን_ጫፍ ላይ ተንጠልጥዬ በጠፍ ጨረቃ ቃጥቼ ደግሞ ዘመንን ቀምረው ሲያመሰጥሩ ተመልክቼ ጻፍ ጻፍ ሲለኝ ከ ሰሜን ባሻገር ባለች በባሩድ ሽታ በተመላች ከተማ ውስጥ ሆኜ እክተብላችሁ ዘንድ ተገደድኩ!

ከለታት በአንዱ ቀን በድንገት ከቤቴ ተነስቼ መጓዝ ጀምርሁ.... ሰው ወደሌለበት፣ ድምጽ ወደ ማይሰማበት፣ ሁካታ ጠብ ክርክር  ንትርክ ወደ ማልሰማበት ወፌ ወደ መራችኝ....!

ስለ እውነት ግን ደክሞኝ ነው.... መኖር ያደክማል አይደል? እልፍ መከራ መስማቱ፣ የተጨነቀች ነብስ ብኩን የሆነችን ስጋ ማየቱ፣ ተስፋ የሌለውን ተስፈኛን መመልከቱ፣ ...ምህረት የማያመጣው ጸሎታችን.. የማያርግ መስዋእታችን... የማን'ባረክበት ብኩርናችን .. ...ነጻ የማያወጣን ትምህርታችን...እያሰብኩ....!

የኢትዮጵያ የነጻነት ቀንዲሉ የሚለኮስበት ቀን አንገት የደፋችው አገር የምትቃናበት ጊዜ የደፈረሰው የሚጠራበት .... ጊዜ ይኖር ይሆን? እላለሁ...! በጠቆረው ዝናባማ ደመና፣ በሚያካፋ የዝናብ ነጠብጣብ፣ ጨርቁን ጥሎ እንደ አበደ ሰው የለበስኩት ፎጦ እየጎተትኩ ...ጯክ ብዬ በምድረበዳ አወራለሁ...!

እላለሁ ...!
'የለህም እንዳልል ይመሻል ይነጋል
አለህም እንዳልል እንዲህ ይደረጋል' 

እላለሁ...!

ተስፋ የተሰጠን ተስፋችን  የት ሄደ? እላለሁ!

የማይነጋBለሊት ስንጠብቅ... እንኖር ዘንድ ተውከን እላለሁ...ነጠብጣቡ ወደ ዶፍ ዝናብ ተቀይሮ መዝነብ ጀመረ... ከመምህሬ አድባር ዛፍ  ስር ከመሰለ ከወዲያ ማዶ ከገደሉ ጫፍ ከተንዘራፋው ዋርካ እጃቸውን የሚያወዛውዙ ሰው ይታዮኛል.....ና ወዲህ ተጠለል በሚመስል ምልክት እየጠሩኝ... 

ወደ ዋርካው ተጠጋሁ ...በል ከዚህ ይሻልሃል ሰላም ሁን ብለው ሲሰናበቱኝ ...መባርቅቱ በበዛበት ብልጭ ልጭታው በጸናበት ስአት የት ሊሄዱ ነው? አልኩ እና መመርኮዣ ዘንጋቸውን ያዝ አደረኩ.... 

ልጄ ሆይ የሰማይ ምሰሶዋ ለቋል፤ 

የምድርም መሰርቷ ተናውጿል.... 

አመጸኛ በዝቷል...
 ሃጥያት ተንሳራፍቷል...
የማያልፈው ዝናብ ከሚመታኝ የሚልፈው ዝናብ ያርጥበኝ ... ልጄ ሆይ ሰማዩን እንዳታየው ማን አይንህን ጋረደህ?! ልቡናህ እንዳያስተውል ማን አዚም አደረገብህ....?!

እኔስ በቀን መሽቶብኛል፣ ከዚህ የባሰው ውሽንፍር ሳይመጣ ወደ ማደርያዬ ልገስግስ...አንተ ግን ሰው ሁን! 

ቀጠሉ..  አመጸናል እና....! 
ምን አልባት እንደ ኖህ ዘመን ዛፉ ተቆርጦ ጉቶ እስኪ ቀር ይቆረጣል... 

መኪና ወዳልገባበት መንገድ ወደ ሌላለበት ልጓዝ .....እንደ ርብ ከመሆን ወሊሃንም ከመምሰል ግን ይሰውረን ልጄ...

ልብህ ከፈቀደ አንተም ሳይመሽ ተከተለኝ .....! 

ይህንን ከአመታት በፊት አልነገርኩህም ወይ የሚል መልእክት በማላቃቸው አረጋዊ ዘንድ ተላከልኝ...!

ለጠቢብ አሃቲ ቃል ትብቁእ ! ለጥበበኛ ሰው አንድ ቃል ትበቃዋለች !
 
በሉ ደና ሁኑልኝ....!

Share on Google Plus

ስለ የተለጠፈበት ቀን

    Blogger Comment
    Facebook Comment