የማይቀረው የኢትዮጵያ ትንሳኤና ዘመኑ ያበቃለት አምባገነን ስርዓት


✍ ቆሞስ አባ ጳውሊ | ከግንባር

ሰሞኑን በመካከለኛው ምስራቅ የተከሰተውን የሰላም እጦት ምክንያት በማድረግ ኢትዮጵያዊያን ከሁለት ጎራ ተከፋፍለው  ሲከራከሩ እያየሁ በጣም እያስገረሙኝ ነበር።  ከምንም በላይ ደግሞ አብይ አህመድ United Arab Emirates ከኢራን የሚሰነዘርበትን የሚሳይል ጥቃት አወገዘ የሚል ዜና ስሰማ በእጅጉ አስገርሞኛል። የራሷ አሮባት የሰው ታማስላለች የሚለው አባባል ምንኛ እውነት ነው! ከጫፍ እስከ ጫፍ ድረስ የኢትዮጵያ ሁኔታ አሁን አሳሳቢ እንደሆነ ሁላችንም እናውቃለን። ሀገሪቱ በታሪክ እንደ አሁን አይነት ፈተና ገጥሟት አያውቅም። አስተዳደራዊ መዋቅሩ በመበላሸቱ ሃገሪቱ በጦርነት እየታመሰች ሲሆን የኑሮ ውድነቱም ህዝቡን እያማረረው ይገኛል። በአሁኑ ሰዓት የኢትዮጵያ ህዝብ በማንኛውም ሁኔታ ተስፋ ቆርጦ ይገኛል።

የመካከለኛው ምስራቅ ጦርነት ለምን እንደተጀመረ አቅጣጫ ከማስቀመጤ በፊት ስለ ኢትዮጵያ መከራና ስለሚሆነው ነገር ልነግራችሁ እፈልጋለሁ። አመናችሁም አላመናችሁም  ወደዳችሁም አልወደዳችሁም ሊሆን ያለው ይሆን ዘንድ ግድ ነው። ኢትዮጵያ በአሁኑ ሰዓት ፈተና ላይ ትገኛለች። ከዘመናት በፊት እናት አባቶቻችን ሲጠብቁት የነበረው ዘመን እነሆ አሁን ነው (መጽሐፈ ኪዳን፣ፍካሬ ኢየሱስ፣ራዕዬ ሲኖዳ፣ፊቅጦር፣ድርሳነ ዑራኤል ፣ራዕዬ ሳቤላ፣ መጽሐፈ ምስጢርና ትርጓሜ ወንጌልን ተመልከቱ::)

በአሁኑ ሰዓት በኢትዮጵያ ላይ እየተካሄደ ያለው ውጊያ በጥልቁ መንፈስ በሚመሩ የሰውን ልጅ የመከራ ቀንበሩን ባከበዱ አምባገነኖችና  የሰውን ልጅ ፍጹም ሰላም ወይንም ትንሳኤ ብለን የምንጠራውን ለማጎናጸፍ  በሚጥሩ በእግዚአብሔር በተመረጡ መካከል ነው።

ኢትዮጵያ አሁን ልክ በእሳት ተፈትኖ ነጥሮ እንደሚወጣ ወርቅ ትልቅ ፈተና ውስጥ ናት።  ከኮሮና ቫይረስ መምጣት በፊት ጀምሮ ይህ ህዝብ  እንዲነቃ ለብዙ ዓመታት ጥረት ሳደርግ ቆይቻለሁ:: ምን መልእክት ሳስተላልፍ  እንደነበር የሰሜን ወሎ በተለይም ደግሞ የላስታና የግዳን ህዝብ ያውቃል። ነገር ግን ይህ ትውልድ አመጸኛ ነው ከመንቀፍና ስም ከመስጠት የዘለለ ምን ምን አያደርግም። በዚህ ሁኔታ ስለሚፈጸመውና ስለሚሆነው ነገር ስማቸውን መጥቀስ የማልፈልገው በርካታ እውነተኛ አባቶች ሰማይ ስሚ ምድርም አድምጭ እያሉ ተናግረዋል። ግን የሚሰማ ትውልድ የለም ሁሉ ነቃፊ ሁሉም ተሳዳቢ ነው። እኛ ተናግረናል ስላልሰማችሁን እሳት እየበላችሁ ነው ወደፊትም ካልሰማችሁ የመከራችሁ ቀንበር ይከብዳል።

ከዚህ አምባገነን ስርዓት ጋር ሆናችሁ የሰው ልጅ መከራ የምታራዝሙ ሁሉ ዋጋ ትከፍላላችሁ። ከህዝብ ጀምሮ የቤተክርስቲያን አገልጋዮችና የመንግስት ባለስልጣናት ሁላችሁም ነፍሳችሁን እና ስጋችሁን የምታድኑበት ሰዓት አሁን ነው። የብልጽግና ስርዓት ይዟችሁ ይጠፋል። በተለይ ደግሞ አገልጋይ አባቶች ንቁ! ጸልዩ፣ መጽሐፍትን አገላብጣችሁ መርምሩ ፣ ስለ ጊዜውም በደንብ ለመረዳት ልቦናችሁን ክፈቱ፣ ነቃፊዎች ብቻም አትሁኑ ለሆዳችሁም አትሙቱ፣ አድርባይም አትሁኑ! ከምድራዊ ንጉስ ይልቅ ሰማያዊውን ንጉስ ፍሩ። አባቶች ይህንን አምባገነን ስርዓት አንድ ሆናችሁ ማውገዝ አለባችሁ::  ቀደምት አባቶቻችን ነገስታትን የማይፈሩ ለእግዚአብሔር ቃልና ለሚጠብቋቸው ምዕመናን የሚኖሩ ነበሩ::  አሁን አሁን የምናያቸው አባቶች በጣም ያሳዝናሉ:: አባቶች ሆይ ህዝብን (ኢትዮጵያን) ወክላችሁ ይህንን አምባገነን ስርዓት መቃወም አለባችሁ:: ይህን ካላደርጋችሁ ዋጋ ትከፍላላችሁ::

ስለሆነም ከመንግስት ጎን ሆነው የሚጨፈጭፉ ማንኛቸውም  ኃይላትና በማንኛውም መንገድ የሚተባበሩ ሁሉ ፍጻሜያቸው የከፋ ነው የሚሆነው። የእግዚአብሔር የፍትህ ሰይፍ ወርዳለች። ኢትዮጵያ እንደወደቀች አትቀርም ትነሳለች። ትንሣኤዋ ተረት ተረት አይደለም በእውነተኛ ልጆቿ በእግዚአብሔር ፈቃድ በቅርብ እውን ይሆናል። ሁላችሁም ወደዳችሁም አልወደዳችሁም የማይቀር ነገር ነው። በዓለም ሁሉ የምትሰሙት የጦርነት ጉሰማ ለኢትዮጵያ ትንሳኤ መቅረብ አመላካች ናቸው። ከኢትዮጵያ ትንሳኤ በኋላ የቀሩት ሃገራት ይናወጻሉ።  ከዚያም ስደት ወደ ኢትዮጵያ ይሆናል የሚባለው ትንቢት ይፈጸማል ማለት ነው። "መልእክተኞችን በባሕር ላይ የደንገል መርከቦችንም በውኃ ላይ ለምትልክ ምድር ወዮላት! እናንተ ፈጣኖች መልእክተኞች ሆይ፥ ወደ ረጅምና ወደ ለስላሳ ሕዝብ፥ ከመጀመሪያው አስደንጋጭ ወደ ሆነ ወገን፥ ወደሚሰፍርና ወደሚረግጥ፥ ወንዞችም ምድራቸውን ወደሚከፍሉት ሕዝብ ሂዱ።በዓለም የምትኖሩ ሁሉና በምድር የምትቀመጡ ሆይ፥ ምልክት በተራሮች ላይ በተነሣ ጊዜ እዩ፤ መለከትም በተነፋ ጊዜ ስሙ።" ትንቢተ ኢሳይያስ ፲፰፥፪

ኢትዮጵያ ከጨለማ ወደ ብርሃን ስትሸጋገር ሌሎች ሀገራት መከራቸው ይከብዳል:: ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ ጽኑ መናወጥ  ምክንያት በርካታ ህዝቦች ወደ ኢትዮጵያ ገብተው ለመጠለል ይለምናሉ። ይህ ከመፈጸሙ በፊት ግን የኢትዮጵያ ትንሳኤ ይጀምራል።  ኢትዮጵያ የመከራው ቀን መሸሸጊያ ናት የሚባለው ለዚህ ነው::  ቅድስት ሀገር ኢትዮጵያን ተራ  አድርጋችሁ የምታስቡ ይህ ምስጢር ሊሰወርባችሁ ተረትም ሊመስላችሁ እንደሚችል አውቃለሁ!  ግን ሊሆን ግድ ነው::

ስለዚህ የኢትዮጵያን ትንሳኤ ለማምጣት ሁላችንም የበኩላችንን ድርሻ መወጣት ይኖርብናል። ከንሰሃ እንዲሁም ከጸሎት ጀምሮ ሀገርንና ሃይማኖትን ለማስጠበቅ ከሚደረጉ  ማንኛውም መልካም የሆኑ እንቅስቃሴዎች ልንሳተፍ ግድ ይለናል።  ኢትዮጵያውያን ንቁ ንቁ ንቁ!

ተንሳኤው አይቀርም ግድ ነው፤ ኢትዮጵያ ታሸንፋለች!l 

Share on Google Plus

ስለ የተለጠፈበት ቀን

    Blogger Comment
    Facebook Comment